
ወልዲያ: ግንቦት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያ የሰሜን ወሎ አሕጉረ ስብከት በሀብሩ ወረዳ ጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምኘ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ አድርጓል። የአህጉረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ድጋፉን በአካል በመገኘት አስረክበዋል።
ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር 2 ሚሊዮን 163 ሺህ ብር ወጭ የተደረገበት ምግብ ነው ድጋፍ ያደረጉት። ብፁዕነታቸው ከዕለት ምግብ በተጨማሪም ለመነኮሳት ቆብ እና ለሙስሊም እናቶች የፀጉር መሸፈኛ ሻርኘ አበርክተዋል። ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ ተፈናቃይ ወገኖችን ሲያጽናኑ ይህ ችግር ያልፋል፤ ነገ ሰርታችሁ ሌሎች ደካሞችን ትደግፋላችሁ ብለዋል፡፡ በተለይ ከቀያቸው በመፈናቀላቸው ከትምህርት ገበታ የራቁ ታዳጊዎች እና ወጣቶች ከመደበኛ ትምህርት ይበልጥ ይህ መከራ የኢትዮጵያን ችግር በደምብ እንዲገነዘቡ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ገልጸዋል። ስለዚህ ማንንም ባለመውቀስ፣ ከበቀል ነጻ በመኾን ኢትዮጵያን ታገለግሏት ዘንድ በየእምነታችሁ ወደፈጣሪያችሁ ጸልዩ ብለዋል።
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ድረስ ከ11 ሺህ በላይ ስደተኞች በጃራ ስደተኞች መጠለያ ካምኘ እንደተጠለሉ ከሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ዘጋቢ፡- ካሳሁን ኃይለሚካኤል
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!