በሰሜን ሸዋ ዞን ያለው የባለሃብቶች ተሳትፎ የሚበረታታ መኾኑን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ተናገሩ።

34

ባሕር ዳር: ግንቦት 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ርእሰ መሥተዳድሩ በሰሜን ሽዋ ዞን ቡልጋ ከተማ አስተዳደር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል በኾነው የኢንሸስትመንት ፎረም ላይ ተገኝተው ከባለሃብቶች እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ውይይት አድርገዋል።

ከአማራ ክልል ጸጋዎች መካከል አንዱ የኾነው የሰሜን ሽዋ ዞን ከሥነ መንግስት ምስረታ፣ ፍልስፍና እና የፊደል ገበታ መነሻነት ባሻገር ታላቅ የሃብት ባለጸጋ መኾኑን ያወሱት የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ዞኑ ለማዕከላዊ ገበያ ቅርብ መኾኑ እና የጂቡቲ የንግድ ኮሪደር ላይ መገኘቱ በርካታ የኢንዱስትሪ ሃብቶች መገኛ እንዲኾን ያስችለዋል ብለዋል።

ይኽን ተከትሎ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በቀጣናው ያለው የባለሃብቶች ተሳትፎ የሚበረታታ እና በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል። ከቡልጋ እስከ ደብረ ብርሃን በተዘረጋው የኢንዱስትሪ ቀጣና ኢንዱስትሪዎች ሥራ ላይ ቢኾኑም በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸውም ርእሰ መሥተዳድሩ አንስተዋል።

ይኽን የርእሰ መሥተዳድሩን ሃሳብ የሚጋሩት በመድረኩ ላይ ሃሳባቸውን የሰጡ ባለሃብቶችም የመሠረተ ልማት አለመሟላት፣ የብድር አገልግሎት በሚፈለገው መጠን አለማግኘት እና የጸጥታ ችግሮች ዘርፉን በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ አድርገውታል ብለዋል። ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በሰጡት ማብራሪያም አካባቢው አሁን ካለበት በተሻለ መልኩ ውጤት እንዲያመጣ እና በባለሃብቶች የተነሱ ጥያቄዎች እንዲፈቱ የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።

በተለይም ኢንዱስትሪዎች በዘመናዊ መልኩ እንዲመሩ ማድረግ እና በባለሃብቱ ላይ የሚያጋጥሙ የመንግሥት ቢሮክራሲዎች እንዲቀንሱ መሥራት አለብን ሲሉ ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል። በተጨማሪም ባለሃብቱ በሥራ እንቅስቃሴው ላይ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ታሳቢ ያደረገ ማኅበራዊ ኀላፊነት ላይ እንዲሳተፉ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አሳስበዋል።

በመድረኩ ላይ በሰሜን ሽዋ ዞን ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደረጉ ባለሃብቶች እና ተባባሪ አካላት ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበምዕራብ ጎጃም ዞን በምርት ዘመኑ ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሠብሠብ ታቅዶ እየተሠራ ነው።
Next articleየሰሜን ወሎ አሕጉረ ስብከት በሀብሩ ወረዳ ጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምኘ ለሚገኙ ወገኖች ድጋፍ አጀረገ።