
ባሕር ዳር: ግንቦት 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል የኾነው እና የሰሜን ሸዋ ዞን የኢንቨስትመንት ፀጋዎች፣ የልማት አገልግሎት ሁኔታ እና ቀጣይ እድሎች ላይ ያተኮረውን መድረክ ከፍተዋል። ዋና አሥተዳዳሪው የሰሜን ሽዋ ዞን ለኢንቨስትመንት ሥራ እምቅ አቅም ያለው መኾኑንም ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ 1 ሺህ 315፣ በአገልግሎት ዘርፍ 797 እና በግብርና ዘርፍ 263 በጠቅላላው 2 ሺህ 375 አልሚ ባለሃብቶች ከ174 ቢሊዮን ብር በላይ በተመዘገበ ካፒታል የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ጠቅሰዋል። በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የምርምር ሥራ የመንዝ በግ፣ የአረርቲ ሽምብራ፣ የምንጃር ማኛ ጤፍ፣ የአንጎለላ ወተት፣ የጅሩ ሰንጋ እና የደብረሲና ቆሎ ብራንድ እንዲያገኙ ተደርገዋል ብለዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት ቡልጋ፣ጨኪ፣ አረርቲ እና ለሚ ከተማ በዋናነት የኢንቨስትመንት መዳረሻ መኾናቸው ለቀጣይ ሥራ መነሻ ኾኖ ሊያገለግል የሚችል እንደኾነም አስረድተዋል። በቡልጋ ከተማም ወደ ምርት የገቡና ዛሬ ያስመረቁ ባለሃብቶች በከተማዋ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ፣ ተጨማሪ ምርት ወደ ገበያ እንዲገባ እና የሥራ ዕድል እንዲፈጠር አድርገዋል ሲሉ ዋና አሥተዳዳሪው አንስተዋል።
በቀጣናው ያለውን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ውጤታማነት ለማረጋገጥ በዘርፉ ማነቆ የኾኑትን የመንገድ፣ የውኃ እና የመብራት መሠረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት ከክልሉ መንግሥት ጋር በጋራ እየተሠራን ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አደራው ምንውየለት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!