ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የአገው ምድር ጠቅላላ ሆስፒታል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

26

እንጅባራ: ግንቦት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እንጅባራ ከተማ በአንድ ባለሃብት ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የአገው ምድር ጠቅላላ ሆስፒታል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ሆስፒታሉን መርቀው የከፈቱት የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የከተማና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ በጤናው ዘርፍ ዘላቂ ግቦችን ለማሳካት የግሉ ዘርፍ ሚና የጎላ መኾኑን ተናግረዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ያሉ የጤና ተቋማት ቁጥር እና ውስጣዊ አደረጃጀታቸው ከኅብረተሰቡ ፍላጎት አንፃር አናሳ መኾናቸውን የገለጹት ምክትል አሥተዳዳሪው የሆስፒታሉ መከፈት ለዚህ ትልቅ አቅም እንደሚኾን ነው ያስረዱት። የሕክምና አገልግሎትን በመንግሥት ሆስፒታሎች ብቻ ተደራሽ ማድረግ አዳጋች ነው ያሉት ምክትል አሥተዳዳሪው የግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል ።

የሆስፒታሉ ባለቤት እና የቦርድ ሠብሣቢ አያና ስማቸው (ዶ.ር) በበኩላቸው ሆስፒታሉ የቀጣናውን ማኅበረሰብ የጤና አገልግሎት ፍላጎት በማርካት ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ታስቦ መከፈቱን ተናግረዋል። ሆስፒታሉ ዘመኑ ባፈራቸው ዘመናዊ መሳሪያዎች እና ልምድ ባካበቱ የህክምና ባለሙያዎች የተደራጀ ስለመኾኑም ባለሃብቱ ገልጸዋል።

ሆስፒታሉን ለመክፈት ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም ተናግረዋል። የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎችም የሆስፒታሉ ሥራ መጀመር ለተሻለ ህክምና ፍለጋ በሚደረገው ጉዞ የነበረባቸውን ወጪና ድካም እንደሚያስቀርላቸውም ነው ያስገነዘቡት። ሆስፒታሉ ከ140 በላይ ለሚኾኑ ባለሙያዎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፍጠሩም ተገልጿል።

ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክር ቤቱ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጸደቀ፡፡
Next articleአያት ሪል እስቴት የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄን በመቀላቀል የ6 ሚሊየን ብር አስተዋፅኦ አደረገ።