ምክር ቤቱ የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጸደቀ፡፡

52

ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 26ኛ መደበኛ ስብሰባ አዲሱን የገጠር መሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀም ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አጽድቋል፡፡ የውሳኔ ሃሳቡን ለምክር ቤቱ በንባብ ያቀረቡት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰሎሞን ላሌ የረቂቅ አዋጁ መሻሻል አስፈላጊነት እና በምርመራው ሂደት የተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር ለጉባኤው አስረድተዋል፡፡

የአርሶ እና አርብቶ አደሮችን እና ከፊል አርብቶ አደሮችን የኑሮ ደረጃ ሀገሪቱ ከደረሰችበት ዘርፈ ብዙ እድገት ጋር እኩል ለማራመድ እንዲቻል፣ የገጠር መሬት ምዝገባ መረጃን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለማደራጀት እና ለተጠቃሚው በአግባቡ ለማሰራጨት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ለመፍጠር ነው፡፡ መንግሥት እና የመሬት ተጠቃሚዎች አስተማማኝ የኾነ መረጃ የሚያገኙበትን ዘመናዊ የመሬት መረጃ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመኾኑ ነው ብለዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የተፈጥሮ ሃብታችንን በዘላቂነት በመጠበቅ እና በማልማት ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ፣ የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የአካል ጉዳተኞች እና ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የመሬት ተጠቃሚነት መብት ማረጋገጥ እና አካታች ሥርዓት መደንገግ አስፈላጊ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ ሰፊ ውይይት የተደረገበት እና በጥልቀት የታየ መኾኑን አንስተዋል፡፡ አርሶ አደሮችን በኪራይ ስም ከመሬት ያለመነቀል መብት፣ ከጋብቻ ጋር የተያያዙ የንብረት ባለቤትነት እና በወል የተያዘ የግጦሽ እና የደን መሬት አጠቃቀምን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

አቶ ሰለሞን የተነሱት ጥያቄዎች ትክክል መኾናቸውን ጠቁመዋል፡፡ መካተት አለባቸው የተባሉ ነገሮችም ማካተት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ የአዋጁን አፈጻጸም በሚመለከት ክልሎች የራሳቸውን ሕግ ስለሚያወጡ የአፈጻጸም ችግር እንደማይኖር ነው ያስረዱት፡፡ በመጨረሻም ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1324/2016 አድርጎ ማጽደቁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ አመላክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዘመናዊ መንገድ የተገነባው የኮምቦልቻ ከተማ መናኸሪያ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
Next articleከ250 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የአገው ምድር ጠቅላላ ሆስፒታል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡