
ደብረ ብርሃን: ግንቦት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በሰሜን ሽዋ ዞን ቡልጋ ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። ከጉብኝቱ ጎን ለጎን የተለያዩ ፋብሪካዎችንም መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
የሰሜን ሽዋ አሥተዳደርም የኢትዮጵያ ታምርት አካል የሆነ የኢንቨስትመንት ፎረም እያካሄደ ነው። በኢንቨስትመንት ፎረሙ የተለያዩ ባለሃብቶች እና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ናቸው። ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የሥራ እንቅስቃሴ በፋብሪካዎች እና በኢትዮጵያ ታምርት ኤግዚብሽን ላይ ምልከታ አድርገዋል።
በፕሮግራሙ ላይ አጠቃላይ የሰሜን ሸዋ የኢንቨስትመንት ጸጋዎች፣ የልማት እና አገልግሎት ሁኔታ እና ቀጣይ እድሎች ላይ ምክክር ይካሄዳል። በቀጣናው ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ድርሻ ላላቸው አካላትም እውቅና ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። በመድረኩ ላይ ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የክልል እና የዞኑ ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ አደራው ምንውየለት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!