
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 09/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል መንግስት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 724 የንግድ ድርጅቶችን ማሸጉን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል።
ጉዳዩ ሁሉንም ነጋዴዎች ባይገልጽም ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ የኑሮ ውድነት እያባበሱ ነጋዴዎች መኖራቸው ኅብረተሰቡን እያማረረ ስለመሆኑ በተከታታይ ስንዘግብ መቆዬታችን ይታወሳል፡፡
በተለይም የታክስ ማሻሻያ የተደረገባቸውን የንግድ ዘርፎችን ምክንያት በማድረግ ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላት የኑሮ ውድነቱን አባብሰውታል።
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጣምያለው ለአብመድ እንደገለጹትም ክልሉ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን እየተቆጣጠረ ነው።
ከሰሞኑ ደግሞ ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ምክንያት በማድረግ ዋጋ የመጨመር አዝማሚያ እየታዬ እንደሆነም ነው አቶ ብርሃኑ የተናገሩት፡፡ በመሆኑም ክልሉ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 724 የንግድ ድርጅቶችን ማሸጉን ገልፀዋል። ይህን መሰል እርምጃ በገበያ አረጋጊው ግብረ ኃይል አማካኝነት ቀጣይነት እንደሚኖረውም አረጋግጠዋል።
በሽታውን ምክንያት በማድረግ ያልተገባ መረጃ የሚያስራጩ “አግበስባሽ ነጋዴዎች” መኖራቸውን የገለፁት ኃላፊው ማኅበረሰቡ ሳይደናገጥ ከዚህ ቀደም በነበረው የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴው ግብይት እንዲፈፅም አሳስበዋል፡፡
የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር ዋናው መፍትሔው አቅርቦትን መጨመር ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ ጠንካራ የሸማቾች ማኅበራትን ለመፍጠር በክልሉ እንደሚሰራም ተናግረዋል። ቢሮው ለሚወስደው እርምጃ ማኅበረሰቡ አጋዥ እንዲሆንም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:-ታርቆ ክንዴ