
ባሕር ዳር: ግንቦት 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምክክሩን የከፈቱት በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በአማራ ክልል ባለፉት 20 ዓመታት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ለግብርና ልማት ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል። አሁን ደግሞ በአነስተኛ ማሳ ላይ ከሰብል ልማት ባሻገር በከብት ማድለብ እና በወተት ልማት እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል። ይሁን እና ያስገኛል ተብሎ ከሚጠበቀው ውጤት አኳያ ሲታይ የሚጠበቅበትን ለውጥ አለማምጣቱን ጠቅሰዋል።
ዶክተር ድረስ መሬትን በአግባቡ በመጠቀም ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ የክልሉን ምጣኔ ሃብት የማሳደግ ተስፋ የተጣለበትን የግብርና ዘርፍ እያጋጠሙት ያሉትን ተግዳሮቶች መርምሮ በተጠናከረ መንገድ የመምራትን አስፈላጊነት ጠቅሰዋል። የክልሉ 80 በመቶ የኾኑ አርሶ አደሮች ያሉባቸውን ማነቆዎች በመፍታት እና የግብርና ሽግግር በማምጣት ከዘርፉ ለሀገር ዕድገት የሚጠበቀውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ሥራ መሠራት እንዳለበትም ተናግረዋል። ውይይቱ ዘርፉ እንዴት እየተመራ እንደኾነ፣ ከየት ወዴት እንደ ደረሰ፣ በቀጣይ የርብርብ መስኮች የሚለዩበት እና በዕቅድ ወደ ተግባር የሚገባበት መነሻ ነውም ብለዋል።
ምክክር ብቻውን በቂ አለመኾኑን እና የችግሩን መነሻ በማወቅ መፍትሄ የማፍለቅን አስፈላጊነት የጠቀሱት ዶክተር ድረስ በአነስተኛ ይዞታ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች በሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ላይ ከሚመረተው ልምድ የመቅሰማቸውን አስፈላጊነት ገልጸዋል። ከአርሶ አደሮች ያነሰ ማምረት ሀገርን የሚጎዳ በመኾኑ ችግሩን ለመፍታት የውይይት መድረኩ ማስፈለጉንም ነው ዶክተር ድረስ የገለጹት። በምክክሩም ችግሩ ተፈትቶ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!