
ከሁሉ አስቀድሜ በዓይነቱም ሆነ በጥራቱ፣ በመጠኑም በውበቱ ልዩ በሆነው፤ የረዥም ጊዜ የሕዝብን ጥያቄ የነበረውን፣ የዚህ ዘመን ትውልድ አሻራ ያረፈበትን፤ የመጪው ዘመን ትውልድ ውርስና ቅርወስ የሆነውን፣ ውብ በሆነ ሁኔታ የተገነባውን ታላቁን ዓባይ ወንዝ ድልድይ በዚህ አኳኋን ተገናኝተን ለመመረቅ በመብቃችን እና በዚህ የምረቃ ሥነ ሥርዓት የደስታችን ተካፋይ ለመሆን ጥሪያችንን አክብራችሁ ለተኛችሁ ክቡራን እንግዶቻችን ከፍ ያለ ምሥጋናየን በአክብሮት አቀርባለሁ፡፡
በፓርቲያችን ብልፅግና የሚመራው መንግሥታችን የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲ በመንደፍ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሌት ከቀን እየተጋ ይገኛል፡፡ ይህ የፓርቲያችን እና የመንግሥታችን ትጋትና ውጤታማነት ከሚገለፅባቸው የልማት ዘርፎች አንዱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸውን መሰረተ ልማት አውታሮችን አስቦና አቅዶ በጥራትና በፍጥነት መፈፀም መቻሉ ነው፡፡ በእኔ አመላካከት ይህ የመሰረተ ልማት አውታር ዝርጋታ የፕሮጀክት ሃሳብ ፅንሰት፣ አተገባበርና ውጤት ቢያንስ ሦስት መሰረታዊ ቁም ነገሮችን ያስተምረናል ብየ አምናለሁ፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ባለፋት ዘመናት ሲጓቱ የነበሩና ወደ ሙት ካፒታልነት ተሸጋግረው የነበሩ እና አገሪቱን ባለዕዳ ያደረጉ ፕሮጀክቶችን ወደ ምንዳዕ የሚቀይር ፕሮጀክት ማከናወንን ያለመ ነው፡፡ ያደሩ ስህተቶችንና ጉድለቶችን የሚያርም፣ ያለፈን በመውቀስ ብቻ ያልተንጠለጠለ፤ የራሱን ዘመን የቤት ሥራ ሠርቶ ለመጪው ትውልድ ምንዳን ለማውረስ ያለመ ሥራ የመፍጠርና የመከወን መክሊት ያለው ፓርቲ የሚመራው መንግሥት የተጎናፀፍን መሆኑን ነው፡፡
ለዚህ ድምዳሜ በርካታ ማሳያዎች ቢኖሩም ማንም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀውን የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን መጥቀሱ በቂ መስሎ ይሰማኛል፡፡ ሁለተኛው ባለንበት ወቅት የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች በትላንት ስሁት ትርክቶች እና በዛሬ አጸፋዊ እርማቶች ላይ ተመስርተው ሕፀጽ እየፈለጉ ለሚራኮቱ ኃይሎች ትምህረት የሚሰጡ መሆናቸው ነው፡፡ ለዚህ ብርቱ ማሳያ የሚሆነው የጋራ ታሪካችንን የሚዘክረው፤ የወደፊት የጋራ ፍላጎታችን የሚበይነውና የሚያፀናውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚዬም መጥቀሱ በቂ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት በነጠላ ትርክት ተቀይደውና በፅንፈኛ አመለካከት ታውረው ለሚደናገሩ ኃይሎች የማንቂያ ደወልም ጭምር ነው፡፡
ሦስተኛ በራሱ ቁሳዊ ወይም መንፈሳዊ ጥቅም የሚስገኙ ብቻ ሳይሆን በትውልዱ ቅብብሎሽ ለሀገር ክብርና የሃብት ምንጭ የሆኑ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ገቢራዊ እየሆኑባት ያለች ሀገር ነች፡፡ ለምሳሌ የጎርጎራ፤ የዓባይ ድልድይን እና በዚህ በጀት የተመጀመረውን የሎጎ ሐይቅን ፕሮጀክት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሀገር ደረጃ እየተገነባ ያለውን ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አገጣጥመን ብልመለከት ምን ያህል የቱሪስት ሃበት ሊኖረን እንደሚችል መገመት አያዳግተንም።
ይህ የምንመለከተው የዓባይ ድልድይ በአጠቃላይ አብዛኛውን የሀገሪቱን ክፍል ከሰሜን ምእራብ ኢትዮጵያ ጋር የሚያስተሳስር በተለይም ደግሞ ለአማራ ክልል ልዩ ፀጋና በረከት ነው ብለን እናምናለን፡፡ ይህ ግዙፍና ውብ ድልድይ የክልላችን ርእሰ መዲና ለሆነችው ባሕር ዳር ቀደምት ምልክቷ ከሆኑት ከጣና ሐይቅ እና ዘንባባ ተክሏ ጋር ተሰላስሎ ዳግም ውብ እና ልዩ መለያ ምልክቷ ሆኖ ይኸው በግርማ ሞገስ ከፊታችን ቆሟል።
ይህ ድንቅ ድልድይ በአንድ በኩል ራሱ የተጠራቀመ ሃብት፤ የጠራ እና ተራማጅ የሆነ ሃሳብ ውጤት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ራሱ ድልድዩ የቀጣዮን ጊዜ ልማት አሳላጭና የልማት የስበት ማዕከል ነው፡፡ በዚህም መደበኛና ከትራንስፖርት ጋር የተሳሰረው ፋይዳው እንደተጠበቀ ሆኖ በድልድዩ በአራቱም ማዕዘናት በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙት አካባቢዎች የመልማት ዕድላቸው ከፍተኛ ሆኗል።
በተለይም ደግሞ ድልድዩን ተንተርሶ ውብና ስነ ምህዳሩን በጠበቀ ሁኔታ የዓባይ ወንዝ ዳርቻ ልማትን ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ማከናወን ግድ በሚለን ሁኔታ ላይ እንድንገኝ ዕድል ፈጥሮልናል። የክልላችን መንግሥትና የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ይህን እድል ሳናባክን ሥራ ላይ በማዋል የሕዝባችንን ተጠቃሚነትና የከተማችንን ውበት በሚያጠብቅ መልኩ አሁኑኑ ወደ ተግባር መግባት ይኖርብናል፡፡
ዕድሜ ለፓርቲያችን እና ለመንግሥታችን ምሥጋና ይግባው እንጂ የክልላችንን ዕድገት የሚያሻሽሉ በርካታ የተጀመሩ መሰረተ ልማት አውታር ፕሮጀክቶች አሉን፡፡ ሆኖም እንዲህ ዓይነት ዘርፈ ብዙ ጥቅምና ፋይዳ ያለውን መሰረተ ልማት አውታሮችን እንዲህ በአማረ ሁኔታ ለማጠናቀቅ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ይፈልጋል፡፡ ይህን ታላቅ ድልድይም ቢሆን እንደማናቸውም የክልላችን ፕሮጀክቶች በክልላችን ያለው በትጥቅ የተደገፈው የነውጥ እንቅስቀሴ በእጅጉ ፈትኖታል፡፡ ይህ ዓይነት የፖለቲካ ፅንፈኝነት የወለደው ነውጥ መንግሥትን ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የግለሰብ እና የማኅበረሰብን የልማት ፕሮጀክት በእጅጉ አስተጓጉሏል፡፡
ዕድሜ ለሀገር መከላከያ ሠራዊታችንና ለክልላችን የፀጥታ አካላት እንዲሁም ለሰላም ወዳዱ ሕዝባችን ምሥጋና ይግባቸውን ዕንፈኞችና ላኪዎቻቸው እንደተመኙት ሳይሆን ታላቁና ባለ ግርማ ሞገሱ የዓባይ ድልድይ እንዲህ በአማረ ሁኔታ ሊጠናቀቅ ችሏል። በተመሳሳይ ሁኔታ በሌሎች የክልላችን አካባቢዎች ታቅደው በፀጥታ መታወክ ምክንያት የተስተጓጎሉ ፕሮጀክቶችም በዋነኛነት በሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲሁም በፊደራልና በክልላችን የፀጥታ ኀይላት ድጋፍ እንደገና እየተጀመሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ እንደጠበቀ ሆኖ ምልዓተ ሕዝቡ በተለይም አርሶ አደራችን በተጨባጭ ጥቅሙ መሰረት በማድረግ (በማዳበሪያ ስርጭትና አጠቃቀም ላይ) በፅንፈኛ ኃይሉ የደረሰበትን ከፍተኛ ጫና ፈንቅሎ እንደወጣ ሁሉ በአካባቢው እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችም የእርሱው ሃብት በመሆናቸውን ተገንዝቦ ከጅማሯቸው እስከ ፍፃሜያቸው ድረስ እንደ ዐይኑ ብሌን ሊጠብቃቸውና ሊንከባከባቸው ይገባል፡፡
ይህ ፕሮጀክት ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱና በክልላችን መንግስት በሕዝባችን ፊት ሊመስገኑ የሚገባቸው የፕሮጀት ሃሳብ ጠንሳሾችና መሪዎች፣ ፈፃሚዎችና አስፈፃማች፣ ባለድርሻና ተባባሪ አካላት አሉ፡፡ ከሁሉ በፊት ለ3 አስርት ዓመታት ሲነሳ የነበረውን የሕዝብ ጥያቄ አዳምጠውና አጢነው ማናችንም ከምንጠብቀውና ከምንገምተው በላይ በመጠንም ሆነ በጥራት፣ በውበቱም በፍጥነት እንዲህ እንጀት በሚያርስ ሁኔታ ፕሮጀክቱን ሃሳብ በመነጭት፣ በጥብቅ ክትትል በመምራት ለአስፈፀሙልን ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) ከፍ ያለ ምስጋና ከታላቅ አክብሮት ጋር አቀርባለሁ! እናነተም አክብሩልኝ፤ አመስግኑልኝ።
በመቀጠል በእራሳቸው የአመራር ዘመን ድልደዩን ያስጀመሩት፣ በየጊዜ በአካል በመገኘት በመከታታል በመደግፍ ለፕሮጀክቱ ፍጻሜ ከፍ ያለ እስተዋፅኦ ለአበረከቱት ለክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስት ለተከበሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከፍ ያለ ምሥጋና አቀርባለሁ፡፡ በሶስተኛ ደረጃ የማቀርበው ምስጋና ሙያተኛ በመመደብ በዬጊዜው የሚለዋወጠውን የገበያና የፀጥታ ችግር ተቋቁመው ፕሮጀክቱን ለዚህ ፍፃሜ እንዲደረስ ላደረገው የቀድሞው የፌደራል መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት የአትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ ለሆኑት ለተከበሩ ኢንጂነር መሃመድ፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸውን እና ለአማካሪ ድርጅቱ ከፍ ያለ ምሥጋና አቀርባለሁ::
ቀደም ሲል ፕሮጀክቱን ለተከታተላችሁና ለመራችሁ የአብክመ ርእሳነ መስተዳድሮች ለተከበሩ አቶ አገኘሁ ተሻገርና ለተከበሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ እንዲሁም ለባሕርዳ ከተማ ከንቲባ ኮሚቴ አባላት፣ ከፍ ያለ ምሥጋና አቀርባሉ፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ታላቅ ድልድይ ግንባታ ላይ ተሳታፊ ለነበራችሁ ባለድርሻና ተባባሪ አካላት ከፍ ያለ ምሥጋና አቀርባለሁ፡፡
አመሠግናለሁ!