“በከተማ አሥተዳደሩ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት እየተዘረጋ ነው” ጎሹ እንዳላማው

57

ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ ክፍለ ከተሞች የሥራ ኀላፊዎች በከተማ አሥተዳደሩ የተሠሩ ሥራዎችን ጎብኝተዋል። ከጎበኙት ውስጥ በ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በፌዴራል መንግሥት በዓባይ ወንዝ ላይ ተገንብቶ የተመረቀው የዓባይ ድልድይ ይገኝበታል። ድልድዩ ለከተማዋ ውበት እና ድምቀት ከመስጠቱ ባሻገር እንደ አንድ መስህብ ኾኖ ሊያገለግል የሚችል ድልድይ መኾኑን የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ገልጸዋል።

በቀጣይ ከጣና ሐይቅ እስከ ጭስ ዓባይ የወንዝ ዳር ልማት ሲከናወን ከተማዋን ይበልጥ ተመራጭ ያደርጋታል ብለዋል። ሌላኛው በሥራ ኀላፊዎች የተጎበኘው በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጭ በመገንባት ላይ የሚገኘው የ8 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መንገድ ነው። መንገዱ 40 ሜትር ስፋት አለው።
በ460 ሚሊዮን ብር ወጭ የተሠራው የጣና ዳር መናፈሻም የጉብኝቱ አካል ነው። አሁን ላይ ደግሞ ሁለተኛው ምዕራፍ 100 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦ እየተሠራ ይገኛል ተብሏል።

የከተማ አሥተዳደሩን ቢሮ የማስፋፋት እና ለሥራ ምቹ እንዲኾኑ የማዘመን ሥራ በጊዜያዊነት እየተሠራ እንደሚገኝም ተገልጿል። የቢሮ ችግሩን ለመፍታት የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ክላስተር እና የአሥተዳደር ግንባታን ያካተተ ዲዛይን መጠናቀቁን ነው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የገለጹት።

ግንባታው 800 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦለታል። ግንባታው 17 ፎቆችን የያዘ ሲኾን በዚህ ዓመትም እንደሚጀምር አስታውቀዋል። በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የመንገድ ዳር ኮሪደር ልማት እንደሚጀምርም ነው የተገለጸው። በከተማ አሥተዳደሩ የሚሠሩ ሥራዎችን እና የሚሰጡ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ለመቆጣጠር እና ለመከታተል በቴክኖሎጅ የታገዘ የአሠራር ሥርዓት እየተዘረጋ ይገኛል ብለዋል።

የባሕርዳር ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ዳዊት የኔው እንዳሉት በከተማ አሥተዳደሩ እየተሠሩ የሚገኙ ሥራዎች ከተማዋን ለኑሮ እና ለቱሪዝም መዳረሻነት ይበልጥ ተመራጭ የሚያደርግ ነው። የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ እና ጥራት እንዲጠናቀቁ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ከግሽዓባይ ክፍለ ከተማ እንደመጡ የነገሩን ጽጌሬዳ አበበ እንዳሉት ደግሞ በከተማ አሥተዳደሩ እየተሠሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የከተማዋን ነዋሪዎች ኑሮ ለማሻሻል ያግዛሉ። ባሕር ዳርን ለማልማት ደግሞ ማኅበረሰቡም ባለቤት መኾን አለበት ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ዜጎች በአጀንዳ መልክ የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች አስፈላጊ መኾናቸውን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
Next articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ ከቢግ ዊን ፊላንትሮፒ መሥራች እና ፕሬዝዳንት ጄሚ ኩፐር እና ቡድናቸው ጋር ተወያዩ።