
ባሕር ዳር: ግንቦት 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኮሚሽኑ ዜጎች በአንጀንዳ ማሠባሠብ ሂደት ውስጥ በንቃት መሳተፋቸው አስፈላጊ እንደኾነ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ገልጿል፡፡ በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ዜጎች በአጀንዳ መልክ የሚያቀርቧቸው ሀሳቦች አስፈላጊ እንደኾኑ ነው ያብራራው፡፡
ዜጎች እና ባለድርሻ አካላት በአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደት ውስጥ በንቃት መሳተፋቸው የውሳኔ ሰጪነትን ለማረጋገጥ እንደሚጠቅም ገልጿል፡፡ ይህ ሂደት ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ እኩል ተሳታፊ እንዲኾኑ ያስችላል ነው ያለው፡፡ ዜጎች በንቃት መሳተፋቸው ሂደቱን ስኬታማ ከማድረጉም በላይ በሀገር ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሰጪነት ሚናን ከፍ እንደሚያደርግ አብራርቷል፡፡
ለተፈጠሩ ችግሮችም የመፍትሔ እርምጃዎችን ለመውሰድ መንገድ ከፋች እንደኾነም ነው ያስገነዘበው፡፡ የሀገራዊ ምክክር በተለያዩ አጋጣሚዎች በሀገራቸው ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብር ውስጥ ድምፃቸው ጎልቶ ያልተሰማ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሀሳቦችን ለማስተጋባት መደላድል ይፈጥራልም ብሏል፡፡ ይህም በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ልምምድ ላይ በጎ ተፅዕኖ ይኖረዋል ነው የተባለው፡፡
በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ዜጎች በእውነት እና በግልፅ የአጀንዳ ሃሳቦቻቸውን ማቅረባቸው የጋራ መተማመንን ለመገንባት ዕድል ይፈጥርላቸዋል ሲልም ገልጿል፡፡ በሂደቱም ሁሉም አካላት ካለፈው ተምረው ስለ ነገዋ የጋራ ሀገራቸው መክረው የማኅበራዊ ውሎቻቸውን ያድሳሉ ብሏል ኮሚሽኑ በማብራሪያው፡፡
ኮሚሽኑ በመላው ዓለም ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው መፃኢ ተስፋ ላይ ጉልህ ሚና በሚኖረው በዚህ የአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደት ላይ ተሳታፊ በመኾን ለዘለቄታው የሚበጁ የመፍትሔ ሀሳቦችን በጋራ ማምጣት እንዲቻል ጥሪ አቅርቧል፡፡ ኮሚሽኑ በመደበኛ መልክ አጀንዳዎችን የሚሠበሥብ መኾኑ እንደተጠበቀ ኾኖ እርስዎ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ ቢነሳልኝ የሚሉትን አጀንዳዎች በቡድን ወይም በግል በፖስታ ሳጥን ቁጥር፡- 32623 አዲስ አበባ በኢሜል፡ ethiopianndc@gmail.com በኮሚሽኑ ድረ-ገፅ፡ https://ethiondc.org.et በመጠቀም ማቅረብ እንደሚችሉም ኮሚሽኑ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ገልጿል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!