
ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አስናቀው ታደለ (ዶ.ር) ኮሌጁ በሙሉ አቅሙ ጥራት ያለው የመምህራን ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል ብለዋል። ብቁ መምህራንን በማፍራትም የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየሠራ ነው።
ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ ከሚነሱ ውስንነቶች አንዱ የመምህራን ሥልጠና ነው ያሉት ዶክተር አስናቀው የትምህርት ጥራትን በሚፈለገው ልክ ለማረጋገጥ ለመምህራን ሥልጠና ተገቢውን ትኩረት እና ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል። በኮሌጁ ከብዛት ይልቅ ጥራት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው ያሉ ሲኾን በአሁኑ ወቅት በየትምህርት ዓይነቱ ለ40 ተማሪዎች ሥልጠና እየሠጠ ነው ብለዋል። በመጪዎቹ ጊዜያት በዓመት ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለመቀበል አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መኾኑንም አብራርተዋል።
በተጨማሪም ከተለያዩ ሀገራት የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸው መምህራን በማምጣት ለአጭር ጊዜ ሥልጠና ለመስጠት ስለመታቀዱንም ነው ዶክተር አስናቀው ያነሱት። ከዚህ በፊት የመምህራን ትምህርት ተበታትኖ በተለያዩ ዘርፍ ነበር የሚሰጠው። ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በተሠራ ሥራ ወደ አንድ ማምጣት ተችሏል።
ተበታትነው የነበሩት ወደ አንድ መምጣታቸው በሥልጠና ሂደቱ ጥራት ያላቸውን ተደራሽ የኾኑ ሥራዎች ለማሠራት እንዲሁም የመምህርነት እሴትን ከመጀመሪያው ጀምረው እያዳበሩ እንዲሄዱ የሚያግዝ መኾኑን አብራርተዋል። ኮሌጁ በመምህራን ሥልጠና የረጅም ጊዜ ልምድ ያካበተ ነው ያሉት ዶክተር አስናቀው የመምህራን ትምህርት ሥልጠና ይበልጥ ለማሻሻል እንዲቻል የሌሎች ሀገራት ልምድ በመውሰድ ምክረ- ሃሳብ በማዘጋጀት ለሚመለከተው አካል ቀርቧል ብለዋል።
ትምህርት ኮሌጁ እራሱን ችሎ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የመኾን ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ መኾኑን ዶክተር አስናቀው ገልጸዋል። በኮሌጁ ሞዴል የኾኑ የመምህራን እና የትምህርት አሥተዳደር ባለሙያዎች ለማብቃት እየተሠራ መኾኑን ጠቁመው፤ በተያዘው በጀት ዓመት በቋንቋ፣ በተፈጥሮ እና ማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ዓይነቶች መምህራንን እያሠለጠነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ዶክተር አስናቀው ኮሌጁ በሁለት ትምህርት ቤቶች እና በሦስት ትምህርት ክፍል ተደራጅቶ እየተሠራ ይገኛል። አገልግሎትን ለማሻሻልም አዲስ ኮምፕሌክስ ህንጻ እየገነባ መሆን ኢፕድ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!