የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖን ጎበኙ።

16

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኀላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በሚሊኒየም አዳራሽ የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ጎበኙ። በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ለአምስት ቀናት ሲካሄድ በቆየው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 210 አምራች ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ያቀረቡ ሲኾን በዛሬው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አምስት ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫዎችን ይዞ በሚያዚያ 2014 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር በመፍታት በሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት ላይ ያላቸው ድርሻ እንዲሻሻል በማድረግ ላይ መኾኑ ተገልጿል። የሀገር ውስጥ ምርት እና አምራቾችን ማጠናከር፣ መሪ ኢንዱስትሪዎችን መፍጠር፣ የኢንዱስትሪ ማኅበረሰብ መገንባት፣ ጥናትና ምርምርን ማሳደግ እንዲሁም ምቹ የቢዝነስ ከባቢን መፍጠር ደግሞ ከንቅናቄው የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ናቸው።

በንቅናቄው የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከነበረበት 47 በመቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ 56 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ነው የተባለው። መንግሥት የተኪ ምርቶች ስትራቴጂ በማዘጋጀት እየሠራ ሲኾን 96 የሚሆኑ ምርቶችን በመለየት በሀገር ውስጥ ለመተካት እየተሠራ ይገኛል። ስትራቴጂው ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ የጸጥታ አካላትን የደንብ ልብስ እና የቢራ ብቅልን ጨምሮ አንዳንድ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ማምረት መጀመሩ ተጠቅሷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት እንዲጠናቀቁ መመሪያ ሰጥቻለሁ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
Next articleየትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለመምህራን ሥልጠና ተገቢውን ትኩረት መስጠት አንደሚገባ ተገለጸ።