
ባሕር ዳር: ግንቦት 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ከአንድ ሺህ 500 በላይ ሙስናን የተመለከቱ ጥቆማዎች መቅረባቸውን የፌዴራል ሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ በኮሚሽኑ የሙስና መረጃ አሥተዳደር መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ፈርዳ ገመዳ ኮሚሽኑ ከፌዴራል ተቋማት እንዲሁም ከክልሎች ሙስና ነክ የኾኑ ጥቆማዎችን እየተቀበለ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት እስካሁን ከክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች አንድ ሺህ 451 ሙስናን የተመለከቱ ጥቆማዎች መቅረባቸውን አቶ ፈርዳ ተናግረዋል። ለክልል የሚደርሱ የሙስና ጉዳዮች ወደ ኮሚሽኑ ሳይደርሱ ከክልሉ የሕግ አካላት ጋር በመኾን እንዲመረመሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡ አቶ ፈርዳ ከፌዴራል ተቋማት በቀጥታ ለኮሚሽኑ ከደረሱት 80 የሙስናን ጥቆማዎች መካከል 65ቱን ጥቆማዎች እና መረጃዎቹን ለፌዴራል ፖሊስ አሳልፎ በመስጠት የማጣራት ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡
ወደ ኮሚሽኑ መረጃ ክፍል ከሙስና ጥቆማዎች በተጨማሪ የተለያዩ የመልካም አሥተዳደር እና ሌሎች ቅሬታዎች እንደሚመጡ ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ኮሚሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 265 ቅሬታዎችን ተቀብሎ ጉዳዩ ወደሚመለከታቸው አካላት መመራቱን አስረድተዋል። ወደ ኮሚሽኑ የሚመጡ ጥቆማዎች ሁሉም የተረጋገጡ የሙስና ወንጀሎች ናቸው ማለት እንደማይቻል እና አንዳንዶች ያለምንም ማስረጃ የግል ጸብን መሠረት ተደርገው የሚቀርቡም እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
አንዳንድ ጥቆማዎች መሠረተ ቢስ በመኾናቸው የኮሚሽኑን የሥራ ሰዓት እያባከኑ በመኾኑ የተረጋገጠ መረጃን ይዞ ጥቆማ ማቅረብ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የኮሚሽኑን የሥራ ኀላፊነት በአግባቡ ካለመገንዘብ የተነሳ ኮሚሽኑ የማይፈታቸውን የተለያዩ ቅሬታዎችን ይዘው የሚመጡበት ሁኔታ ሌላኛው ችግር እየፈጠረ የሚገኝ ጉዳይ መኾኑን አንስተዋል፡፡
አቶ ፈርዳ በሀገሪቱ የሙስና ፈጻሚዎች ጉዳይ አሁንም አሳሳቢ መኾኑን በየጊዜው እየተሠሩ ያሉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙ ገልጸዋል፡፡ ኅብረተሰቡ ከሙስና ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለመስጠት ያለው ተባባሪነት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ሙስና ሀገርን የሚጎዳ ጸያፍ ተግባር መኾኑን በመረዳት ሁሉም ዜጋ ለሕገ ወጥ ድርጊቱ ተባባሪ ባለመኾን እና ሙስና ፈጻሚዎችን ለይቶ በማውጣት ተሳትፎውን ማሳደግ እንዳለበት ኢፕድ ዘግቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!