“ዝግጅታችን አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ነው” የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች

208

ባሕር ዳር: ግንቦት 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ከተለመደው የፈተና አሰጣጥ በተለየ መልኩ መስጠት ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በአዲሱ የፈተና አሰጣጥ ሂደት ታዲያ ብዙ አዳዲስ ነገሮች ተፈጥረዋል፡፡ አዲሱ የፈተና አሰጣጥ ኩረጃ እንዲቀንስ እና ተማሪዎች ራሳቸውን ችለው እንዲያልፉ የሚያደርግ መኾኑ ይነገርለታል፡፡

የውጤት ማሽቆልቆል በገጠመበት ዓመታት የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ሁሉንም ተማሪዎቻቸውን በማሳለፍ እና ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ልዩ ኾነው ወጥተዋል፡፡ በትምህርት ቤቶቹ የተመዘገበው ውጤት አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ የማንቂያ ደወል ደውሏል፡፡

በደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪው ይከበር ግዛቸው ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት እየተዘጋጀን ነው ብሏል፡፡ የመምህራን አስተዋጽኦ እና ለፈተና ዝግጁ እንድንኾን የሚያደርጉት ድጋፍ የሚደነቅ ነውም ይላል፡፡ በደሴ ከተማ ያለው ሰላም ለመማር ማስተማሩ ምቹ መኾኑንም ተናግሯል።
ትምህርት ከተጽዕኖ ነጻ ኾኖ ትኩረትን ይሻል ነው ያለው፡፡ ለመምህራን ጥረት ስል ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት ጥረት አደርጋለሁ፤ ጥሩ ውጤት ለማምጣት እዘጋጃለሁ፣ ቀጣይ ያሉት ወራት ደግሞ የበለጠ ያግዙናል ብሏል፡፡

ሌላኛው የ12ኛ ክፍል ተማሪ አሸናፊ ፋንታሁን ትምህርት ቤቱ ቀድሞ በመጥራቱ ለመማር ማስተማሩ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል ነው ያለው፡፡ ዝግጅታቸው በጥሩ ሁኔታ እየቀጠለ መኾኑንም አንስቷል፡፡ በትምህርት ቤቱ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ውጤቶች መነሳሳትን ይፈጥራሉ፣ ትምህርት ቤቱ፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ የአማራ ክልል ሕዝብ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከእኛ ላይ ተስፋ ይጥላል፤ የተጣለብን ተስፋ እውን ለማድረግ በርትተን እያጠናን ነው፣ በእኛ ትምህርት ቤት የሚያሳስበው ማለፍ አለማለፍ አይደለም፣ ጥሩ ውጤት ማምጣት ነው እንጂ፣ ትምህርት ቤቱ ላይ አለማለፍ የሚባል ነገር አይታሰብም፣ ከእኛ ደግሞ ብዙ ነው የሚጠበቀው፣ ከፍተኛ ውጤት ይጠበቅብናል፤ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በተለይም የባዮሎጂ ትምህርት ትንሽ ጠጠር ይላል፤ ያም ኾኖ ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ ነው የምንሠራው ነው ያለው፡፡

ዝግጅታችን ታሪኩን ለማስቀጠል ብቻ አይደለም፤ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ነው ብሏል፡፡ ንድፈ ሃሳብን ከተግባር ጋር እያጣመሩ እንደሚሠሩም አመላክቷል፡፡ ሌሎች ተማሪዎችም በቁርጠኝነት በመዘጋጀት ስኬታማ የኾነ ውጤት ማምጣት አለባቸው ነው ያለው፡፡ “የውኃ ጠብታ ድንጋይ ይሰብራል” ያለው ተማሪው በየቀኑ ያለ ማቋረጥ ጥቂት ጥቂት መዘጋጀት በመጨረሻም ውጤታማ ያደርጋል ይላል፡፡

በደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የባዮሎጂ ላቦላቶሪ መምህርት ፋጡማ ዓሊ ሁሉም ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ መምህራን ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡ ከክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ለትምህርት ቤቱ ተከታታይ የኾነ ድጋፍ ባይደረግም ችግሮችን ተቋቁሞ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ተማሪዎችን እያዘጋጀ ነው ይላሉ፡፡

ተማሪዎች ለብሔራዊ ፈተና ያላቸው ዝግጅት እና ትጋት የሚደነቅ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ከመምህራን ጋር ያላቸው ግንኙነትም ቤተሰባዊ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ ሁልጊዜም ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት ትምህርት ቤቱን መደገፍ ይገባልም ብለዋል፡፡ ከፍተኛ የኾነ የተማሪዎች አቅም መኖሩንም ገልጸዋል፡፡ በተማሪዎቻችን ወደፊትም እንኮራለን ነው ያሉት፡፡ የመምህራን እና የተማሪዎች ጥረት እና መልካም ግንኙነት ከቀጠለ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የባዮሎጂ መምህሩ ዓለማየሁ ደጀኔ ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ጋር በተያያዘ የባዩሎጂ ትምህርት ሰፊ እና አድካሚ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ይሄም ተማሪዎች በቀላሉ ለመረዳት ፈተና ኾኖባቸው መቆየቱን እና ለመምህራንም ፈታኝ እንደነበር ነው ያነሱት፡፡ ነገር ግን በተደረገው ጥረት ትምህርቱን በሚገባ መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ በርካታ ጥያቄዎችን እያወጡ መስጠታቸውንም ተናግረዋል፡፡ አስተማማኝ እና ተስፋ የሚጣልባቸው ተማሪዎች መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡

መምህራን ከልባቸው ማስተማራቸው፣ ተማሪዎችም ተግተው በመሥራታቸው ምክንያት ባለፉት ዓመታት ጥሩ ውጤት መመዝገቡን አስታውሰዋል፡፡ የመምህራን እና የተማሪዎች ብርታት ለዘንድሮው የብሔራዊ ፈተናም መቀጠሉን ነው የተናገሩት፡፡ የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር በለጠ ኃይሌ የባለፉት ዓመታት ስኬቶችን ለማስቀጠል ከፍተኛ ዝግጅት ላይ ነን ብለዋል፡፡ መምህራን አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ከነባሩ ጋር በማዛመድ እንደሚያስተምሯቸውም ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎች በተደጋጋሚ ፈተናዎችን ይሰጣሉ፣ ፈተናዎችን ሠርተው በጋራ ያርማሉ። ይኽ ደግሞ ተማሪዎች ከፍተኛ ዝግጅት እንዲያደርጉ እና ውጤታቸው ያማረ እንዲኾን ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

መምህራን አብቲቲዩድ የሚል ክፍለ ጊዜ ፈጥረው ከሒሳብ እና ከእንግሊዝኛ ትምህርት ዓይነቶች በሚገባ እንደሚያስተምሯቸው ነው የተናገሩት፡፡ ይህ ልምድ በሌሎች አለመኖሩንም አንስተዋል፡፡ ዝግጅታችን ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ውጤት ለማምጣት ነው ብለዋል ርእሰ መምህሩ፡፡
በሚቀጥሉት ወራት ከፍተኛ ዝግጅት እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡ ከሚፈተኑት ተማሪዎች ቢያንስ 50 በመቶ የሚኾኑት ከስድስት መቶው አምስት መቶ እና ከዚያ በላይ ያስመዘግባሉ የሚል ግብ አስቀምጠው እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በጣም ዝቅተኛ የኾነ ተማሪ ከ450 በታች አይወርድም የሚል ግብ አለን ነው ያሉት፡፡

የተሰጣቸው የቤት ሥራ እና አደራ በኢትዮጵያ የቀደመውን ክብረ ወሰን እንዲሰብሩ እና አዲስ ክብረ ወሰን እንዲያስመዘግቡ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የመምህራን ብርታት እና ጉብዝና ለከፍተኛ ውጤት ያበቃል ያሉት ርእሰ መምህሩ በትምህርት ቤታቸው ያሉ መምህራን የተመረጡ እና ጎበዞች መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ለተማሪዎቻቸው የሚገባቸውን ነገር እንደሚያስተላልፉ ገልጸዋል፡፡ በደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የማይሸፈን የትምህርት ምዕራፍ የለም ነው ያሉት፡፡ ለተማሪዎች የመዘጋጃ ጊዜ መስጠትም ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ለተማሪዎች ከፍተኛ ቁጥጥር እና ክትትል እንደሚደረግላቸውም ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ምሥጋና አቀረቡ።
Next articleበሀገሪቱ የሙስና ፈጻሚዎች ጉዳይ አሁንም አሳሳቢ መኾኑ ተገለጸ።