
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) ምሥጋና አቅርበዋል።
ሙሉ መልእክቱ ቀጥሎ ቀርቧል፦
ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተፈጥሮ ፀጋ የታደለችውን እና የተፈጥሮ ውበቷን የበለጠ ፍንትው አደርጎ በማውጣት የቱሪስት መዳረሻ ለመኾን የወርቃማ ዕድል ባለቤት በኾነችው ጎርጎራ፤ ከብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመኾን ስለሀገር ክብር እና ስለሕዝብ ጥቅም በዝርዝር ከመከሩ በኋላ ግንቦት 4/2016 ዓ.ም የሁሉም ክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች እና ሚኒስትሮች በተገኙበት በውቢቷ ባሕር ዳር ከተማ በመገኘት በዓለማችን ትልቁ ወንዝ በኾነው ዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባውን ታላቁን ድልድይ መርቀው ሥራ አስጀምረውልናል። ለዚህ በጎ ተግባርዎ፤ በታላቁ የክልላችን ሕዝብ እና በአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ስም ምሥጋናዬን በታላቅ አክብሮት አቀርባለሁ።
በዚህ ታሪካዊ ወቅት ለክልላችን ሁለንናዊ ልማት እና ሰላም መረጋገጥ ይበጅ ዘንድ በታላቁ የዓባይ ድልድይ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝታችሁ የአበረታታችሁን ክቡራን ርእሳነ መሥተዳድሮች፣ ክቡራን ሚኒስትሮች እና ሌሎች የፌደራል መንግስት የሥራ ኀላፊዎች ስለአደረጋችሁልን ሁሉ እጅግ እናመሠግናለን።
እጅግ ለተከበራችሁ እና እንግዳ ተቀባይነት መገለጫችሁ ለሆነው የባሕር ዳር እና አካባቢዋ ነዋሪዎች በሙሉ በፀረ ሰላም ኀይሎች የነበረባችሁን ጫና ከምንም ሳትቆጥሩ በምረቃ ቦታው በመገኘት እና እንግዶችን በመቀበል ላሳያችሁት ፍቅር እና አክብሮት በራሴ እና በክልላችን መንግሥት ስም ከፍ ያለ ምሥጋናየን አቀርባለሁ።
የተከበራችሁ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች፤ እንደዚህ ዓይነቶቹ ዘመን ተሻጋሪ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ ዛሬ እንዳሳያችሁት አንድነት እና ኅብረት ሁሉ ከተማችን የበለጠ ሰላሟና ልማቷ እንዲረጋገጥ በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት አመራሮች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ እንድትሠሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
በጫካ ለምትገኙ ወንድሞቻችንም በእውነት ከክልላችን ሕዝብ ጥቅም እና ክብር ውጭ ሌላ ስውር አጀንዳ ከሌላችሁ በስተቀር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) ባቀረቡላችሁ ጥሪ መሠረት ችግሮቻችንን በውይይት እና በድርድር እንድንፈታና ሕዝባችንም እፎይታ እንዲያገኝ በድጋሜ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
በመጨረሻም መላ የክልላችን ሕዝብ በክልላችን የተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም የበለጠ ስር እንዲሰድ እና የልማት ሥራዎች ሳይስተጓጎሉ የበለጠ ተጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ የማይተካ ሚናህን እንድትወጣ በድጋሜ ጥሪየን በአክብሮት አቀርባለሁ።
ሰላም ለክልላችን፤ አንድነት ለሕዝባችን!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!