“ታላቁ ድልድይ ለከተማዋ ልዩ ድምቀት እና ስጦታ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

61

ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በታላቁ የዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ታላቁ ድልድይ ተመርቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የዘመናት የሕዝብ ጥያቄ የነበረው ድልድይ በፌዴራል መንግሥት ተቀባይነት አግኝቶ፣ ወጪውም በፌዴራል መንግሥት ተሸፍኖ ተሠርቶ በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አለን ብለዋል። ይሄን የትውልዶች ስጦታ የኾነ ድልድይ ለከተማችን፣ ለክልላችንና ለሀገራችን ስለተበረከተልን ከልብ እናመሰግናለን ብለዋል።

ባሕር ዳር ለጎብኚዎች፣ ለነዋሪዎች፣ ለአልሚዎች ተመራጭ የኾነች ከተማ መኾኗንም ተናግረዋል። ከተማዋ የቱሪዝም እና የኢንዱስትሪ ከተማ መኾኗንም አስታውቀዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች እንግዳ ተቀባይ፣ ሰላም ወዳድ፣ ልማት እና እድገት ፈላጊ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት እና ኢትዮጵያዊነት የማይናወጥ ከልብ የመነጨ ፍቅር ያላቸው ናቸው ብለዋል።

በታላቁ የዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ታላቁ ድልድይ ዝም ብሎ ድልድይ ብቻ ሳይኾን ከድልድይ ባሻገር የኾነ መኾኑን ነው የተናገሩት። ድልድዩ በፈተና አልፎ ለዚህ የደረሰ መኾኑንም አንስተዋል። ድልድዩ በኢትዮጵያ ፖለቲካና ታሪክ ልዩ ቦታ ባለው የዓባይ ወንዝ ላይ መገንባቱ ለየት የሚያደርገው መኾኑንም ገልጸዋል። ማድረግ እንችላለን የሚለውን ደጋግመን ያሳየንበት ነውም ብለዋል።

ለከተማዋ ከውበት በላይ ውበት ያጎናጽፋታል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ለከተማዋ ልዩ ድምቀት እና ስጦታ ነውም ብለዋል። ድልድዩ ለከተማዋ እንደ አንድ የቱሪስት መዳረሻ ኾኖ እንደሚያገለግልም አመላክተዋል። ክልሉ ባጋጠመው የፀጥታ ሁኔታ የከተማዋ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ተቀዛቅዞ እንደነበር ያስታወሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሰላም ወዳዱ የከተማዋ እና የክልሉ ሕዝብ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በሠራው ሥራ የፀጥታ ሁኔታው መለወጡን አስታውቀዋል። በከተማዋ መደበኛ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል።

የከተማ አሥተዳደሩ በራሱ አቅም 22 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የአስፓልት እና 4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ እያሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። የፌዴራል ፕሮጄክቶችም ሳይቆራረጡ መቀጠላቸውን ነው የገለጹት። በውቧ ከተማ ጥቂት መዋለ ንዋይ አፍስሶ ብዙ ማግኘት እና ማትረፍ እንደሚቻልም ተናግረዋል።

ከድልድዩ በላይ እና በታች የዓባይ ወንዝ ዳር፣ የቤዛዊት ቤተ መንግሥት ልማት አስፈላጊ በመኾናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረት እንዲያደርጉባቸው ጠይቀዋል። ያልተቆጠበ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኦቪድ ግሩፕ ለጽዱ ኢትዮጵያ የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
Next articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እና ከፍተኛ መሪዎች በጽዱ ኢትዮጵያ ቴሌቶን ላይ በጋራ ተሳተፉ።