
ባሕር ዳር: ግንቦት 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በታላቁ የዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው ታላቁ ድልድይ ተመርቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሙሐመድ አብዱራህማን ድልድዩ 380 ሜትር ርዝመት እና 43 ሜትር ስፋት ያለው መኾኑን ገልጸዋል። በግራ እና በቀኝ በአንድ ጊዜ ስድስት ተሽከርካሪዎችን ማስተላለፍ ይችላል ብለዋል። ድልድዩ የቤዛዊት ቤተ መንግሥትን እንደሚያስተሳስርም ተናግረዋል። ድልድዩ መሠረታዊ ጥገና ሳይጠይቅ ከመቶ ዓመታት በላይ እንዲያገለግል ተደርጎ እና ጥራቱን ጠብቆ የተገነባ መኾኑንም አስታውቀዋል።
ከ54 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ አርማታ፣ ከ90 ሺህ ቶን በላይ ብረት፣ ከ500 ቶን በላይ መወጠሪያ ገመዶችን እንደዋና ግብዓት መጠቀሙንም ገልጸዋል። ዲያሜትራቸው 1 ነጥብ 8 ሜትር የኾኑ፣ ከመሬት በታች 24 ሜትር ጥልቀት ድረስ የተቀበሩ 88 መሠረቶች ላይ የቆመ መኾኑንም አስታውቀዋል።
የድልድዩ የላይኛው ክፍል በ72 ኬብሎች የተወጠረ ነው ተብሏል። ጠቅላላ ክብደቱ በኬብሎቹ አማካኝነት ወደ ቋሚ ምሰሶዎች እንዲተላለፍ ተደርጎ ከምሰሶው ወደ መሠረቱ እንዲዘልቅ ተደርጎ የተሠራ መኾኑንም አንስተዋል። አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተሠራ ድልድይ መኾኑንም ገልጸዋል። የትራፊክ ፍሰቱን ከማሳለጥ ባሻገር የተለያየ መስተጋብር መስጠት የሚችሉ መብራቶች የተገጠሙለት መኾኑ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ከተሠሩ ድልድዮች የተለየ ያደርገዋል ነው ያሉት።
ድልድዩ በቻይና ኮምዩንኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ መገንባቱንም አመላክተዋል። ለድልድዩ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል። 4 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር መንገድም እንዳለውም አንስተዋል። ድልድዩ የተለያዩ ትምህርታዊ ጉብኝቶች እንደተደረጉበት የተናገሩት ዳይሬክተሩ ገብኚዎቹ እውቀትን ቀስመውበታል፣ ለቀጣይ ትውልድ መማሪያ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚኾን እምነቴ ነው ብለዋል። ለድልድዩ ግንባታ መሳካት ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል። ጥራቱን እና ውበቱን ጠብቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ሕዝቡ ጥበቃ እንዲያደርግለትም አደራ ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!