“በታላቁ ወንዝ የተገነባው ታላቁ ድልድይ ለአማራ ክልል ልዩ ጸጋና በረከት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

39

ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በታላቁ ወንዝ የተገነባው ታላቁ ድልድይ ተመርቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ድልድዩ በአይነቱም ኾነ በጥራቱ፣ በመጠኑም ኾነ በውበቱ ልዩ ነው ብለዋል። ድልድዩ የረጅም ጊዜ የሕዝብ ጥያቄ እንደነበርም አስታውሰዋል። የዚህ ዘመን ትውልድ አሻራ ያረፈበት፣ የመጪው ዘመን ትውልድ ወርስና አደራ የኾነውን፣ በታላቁ ወንዝ ላይ የተገነባውን ታላቁን ድልድይ በመመረቃችን ደስታችን ላቅ ያለ ነው ብለዋል።

ድልድዩ የቀጣዩን ጊዜ ልማት አሳላጭ እና የልማት የስበት ማዕከል መኾኑንም አንስተዋል። ከመደበኛ ትራንስፖርት ፋይዳው ባሻገር በድልድዩ አራቱም ማዕዘናት የሚገኙ አካባቢዎችን የመልማት እድል ከፍ እንዲል አድርጓል ነው ያሉት። ውበትና ሥነ ምሕዳሩን በጠበቀ ሁኔታ ለዓባይ ወንዝ ዳርቻ ልማትን ለማከናወን እድሉን እንደፈጠረም ገልጸዋል።

የሕዝብ ተጠቃሚነት እና የከተማዋን ውበት በሚጠብቅ መልኩ አሁንኑ ወደ ተግባር መግባት ይኖርብናል ነው ያሉት። እንዲህ አይነት መሠረተ ልማቶችን ሠርቶ ለማጠናቀቅ አስተማማኝ እና ዘለቂ ሰላም እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የጸጥታ አካላት ምስጋና ይግባቸውና ጽንፈኞች እና ላኪዎቻቸው እንደተመኙት ሳይኾን ታላቁ ድልድይ ተመርቋል ነው ያሉት። በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተስተጓጉለው የነበሩ ፕሮጄክቶች እንደገና መጀመራቸውንም አስታውቀዋል።

መላው የክልሉ ሕዝብ በክልሉ በተለያዩ ሥፍራዎች እየተገነቡ ያሉ ፕሮጄክቶችን እንደ ዓይኑ ብሌን ሊጠብቃቸው ይገባል ብለዋል። ፕሮጄክቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለተጉ ሁሉ ምስጋናም አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ የሚገባትን፣ የአማራ ሕዝብ የሚገባውን፣ ባሕር ዳርም ለውበቷ የሚመጥን ታላቁን ሥራ በጋራ ለማስመረቅ በቅተናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleአቶ ያደታ ጁኔዲ ለ#ጽዱኢትዮጵያ ዲጂታል ቴሌቶን የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረጉ።