“ኢትዮጵያ የሚገባትን፣ የአማራ ሕዝብ የሚገባውን፣ ባሕር ዳርም ለውበቷ የሚመጥን ታላቁን ሥራ በጋራ ለማስመረቅ በቅተናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

66

ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በታላቁ ወንዝ የተገነባውን ታላቁን ድልድይ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ድልድዩ ወገን ከወገን፣ ቤተሰብን ከቤተሰብ፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያገናኝ ንግድ የሚያሳልጥ በሰዎች አዕምሮ የታሰበ፣ ገንዘብ፣ ጉልበት ዕውቀት የፈሰሰበት ነው ብለዋል። እኛ ሁለት ድልድይ መገንባት እንፈልጋለን፣ ድልድዩን እንገነባለን፣ የሕዝቦችንን አንድነት እናረጋግጣለን የምንለው በድንጋይ እና በሲሚንቶ የሚሠራ ድልድይ ብቻ ሳይኾን በትርክት በሚገነባ የአብሮነት ድልድይም ጭምር ነው ብለዋል።

“ኢትዮጵያ የሚገባትን፣ የአማራ ሕዝብ የሚገባውን፣ ለባሕር ዳርም ውበት የሚመጥን ታላቁን ሥራ በጋራ ለማስመረቅ በቅተናል” ሲሉ ተናግረዋል። በሕዝቦች መካከል በነበሩ አልባሌ ትርክቶች ምክንያት እየላላ ያለውን ትስስር ሊያጠናክር የሚችል የትርክት ድልድይ መገንባት እንፈልጋለን ነው ያሉት። ውቡ እና ትልቁ ድልድይ እኛነታችንን፣ ፍላጎታችንን፣ መሻታችንን ያሳያል ብለዋል።

በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ብልጽግናን እንመኛለን ስንል በንግግር ያልተገነዘቡን ሰዎች በዚህ ድልድይ ብልጽግና ማለት ምን ማለት እንደኾነ እንዲረዱ እፈልጋለሁ ነው ያሉት። ብልጽግና ለዛሬ ሳይኾን ለትውልድ የሚሠራ፣ በኢትዮጵያ ልክ ትልቅ አድርጎ የሚሠራ፣ ለሕዝቡ የገባውን ቃልና በተግባር ያስጀመረውን በማስጨረስ የሚያረጋግጥ ነውም ብለዋል።

በአማራ ክልል ያልተቋጨውን የመገጭን ፕሮጀክት ጨምሮ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶችን መጨረስ የማይቻለው ከልብ፣ ይሁን ተብሎ እና በመከታተል ስለማይሠራ ነው፣ ዛሬ ያን እሳቤ የሚሰብር፣ በከፍተኛ ጥራት፣ ፍጥነት እና ለትውልድ በሚሻገር ልክ የተሠራውን ድልድይ አስመርቀናል ነው ያሉት።

ታላቁ የአማራ ሕዝብ በጥልቀቱ ልክ ራሱን አልምቶ፣ ራሱን አሻሽሎ ከችግር የወጣ እንዲኾን ትብብር እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። እኛ ለዚህ ትልቅ ሕዝብ ያለን መሻት እና ፍላጎት አንድነቱን፣ ሰላሙን ጠብቆ፣ ልማቱን ማረጋገጥ እንዲችል ነው ብለዋል። “በጫካ ለሚገኙ ወንድሞቻችን ጥሪ ላቀርብላቸው እፈልጋለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ አማራ መሪ አግኝቷል፤ አረጋ ከበደን የመሠለ ታማኝ ትጉህ መሪ አግኝቷል፣ አማራ ነኝ፣ ለአማራ እቆረቆራለሁ የሚል፣ የአማራ ጥቅም ሊነካ አይገባውም የሚል፣ አማራ በልኩ መጠቀም አለበት የሚል፣ ስለ አማራ መብት፣ ስለ አማራ ዲሞክራሲ የሚታገል ማንኛውም ግለሰብ እና ቡድን ሰክኖ በማሰብ ሕዝቡን እና ክልሉን መጥቀም ስለሚችል ይብቃን መገዳደል፣ ይብቃን ጥፋት፣ ይብቃን አላስፈላጊ እና የማያሻግር ጉዞ፣ ድልድይ የሌለው ጉዞ፣ ኢትዮጵያን አንድ የማያደርግ ጉዞ፣ የኢትዮጵያን ሕዝቦች በእኩል የማያከብር ጉዞ ስለማይጠቅመን ኑ ወደ ክልላችሁ ተመለሱ፣ ክላችሁን አልሙ፣ ሰላማችሁን ጠብቁ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ያን ስታደርጉ እኛም በሙሉ ልብ ከጎናችሁ ኾነን አብረናችሁ እንሠራለን፣ በማይገባ ነገር መገዳደል ይብቃል ልላቸው እፈልጋለሁ” ነው ያሉት።

“ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት፤ በብዙ ዓይነት ቁርሾ ቆይታለች፣ አሁን የሚያስፈልገን ነፃነት፣ አሁን የሚያስፈልገን ወንድማማችነት፣ አሁን የሚያስፈልገን መከባበር፣ እኩል ዜጋ ኾኖ ኢትዮጵያን በጥረት መገንባት ነውና ሕልማችን እውን እንዲኾን ከቀልባቸው እንዲመለሱ፣ ልቦናቸውን እንዲያዳምጡ፣ ይህችን ታላቅ ሀገር ክብሯን ጠብቀን ለልጆቻችን ማሻገር እንድንችል ከጎናችን እንድትኾኑ ለአማራ ሕዝብ እና መንግሥት አደራ ማለት እፈልጋለሁ” ብለዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር መሪዎች ያማያልፍ አሻራ እንዲያኖሩ አደራ ብለዋል። ኢትዮጵያን የሚመጥን ድልድይ በውቧ ከተማ ማስቀመጥ ለቻሉ ባለሙያዎች እና መሪዎች ምስጋና አቅርበዋል። በምሥራቅ አፍሪካ ካልተጋነነ በመላው አፍሪካ ተወዳዳሪ የማይገኝለትን ድንቅ የጎርጎራ ፕሮጀክት ለሁለት ቀናት ማሳለፋቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጎርጎራን ያክል ጠንካራ፣ ውብ እጅግ አስደማሚ ሥራ እስካሁን አላየንም ነው ያሉት። የጎርጎራን ፕሮጀክት እንዲያዩ እና እንዲጠብቁ አደራ ብለዋል። ብዙ የምንጀምረው እና የምናጠናቅቀው ሥራ አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን ኾኖ እንዲያግዝም ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽዱ ኢትዮጵያ ጽዱ ከተማ ለመገንባት በአንድ ጀምበር 50 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ እየተሠራ ባለው ሥራ ሁሉም እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው በተገኙበት የዓባይ ድልድይ ተመረቀ።
Next article“በታላቁ ወንዝ የተገነባው ታላቁ ድልድይ ለአማራ ክልል ልዩ ጸጋና በረከት ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ