
ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ለማሳደግና ተወዳዳሪ ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ መኾኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ተናገሩ። በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ከተከፈተው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በተጓዳኝ “ጥናትና ምርምር ለተሻለ ለአቅም ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ለማሳደግና ተወዳዳሪ ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም በተለይም ከትምህርት ተቋማትና በዘርፉ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር በቅርበትና በትብብር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅምና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ዘርፉን በጥናትና ምርምር መደገፍ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በእውቀትና በክህሎት የዳበረ የሰው ኀይል በማሰማራት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ደግሞ የትምህርት ዘርፍ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው ለአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ውጤታማነት የትምህርት ዘርፉ የላቀ ሚና ይጠበቅበታል ብለዋል። ለዚህም የትምህርት ጥራት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለዘርፉ ልማት ችግር ፈችና ቀጣይነት ያለው ጥናትና ምርምር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!