“ የባሕርዳር ውበት፤ የግዮን ሰገነት”

91

ባሕር ዳር: ግንቦት 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ብዙዎች በዋና ተሻግረውታል፤ ብዙዎች በገመድ ተንጠልጥለው አቋርጠውታል፤ ገሚሶች በታንኳ አልፈውታል፤ ብዙዎችም ክረምቱ እስኪያልፍ፣ ማዕበሉ እስኪጎድል ማዶ እና ማዶ ኾነው ጠብቀውታል፤ ግዮን እስኪጎድል፣ ውኃው እስኪጠል ድረስ በናፍቆት ከርመዋል፤ የቅርብ ሩቅ ኾነው ኖረዋል፡፡ ለናፍቆታቸው ዜማ እያዜሙ፣ ቅኔ እየተቀኙ ጊዜውን አሳልፈዋል፡፡

“አንቺ ወዲያ ማዶ እኔ ወዲህ ማዶ አንገናኝም ወይ ገደሉ ተንዶ” እያሉ ያዜሙትም ብዙዎች ናቸው፡፡ ግንቦት ሲዳምን፣ የሰኔ ሰማይ ሲጠቁር፣ የክረምቱ ዝናብ በኃይል ሲጥል የግዮን ገባሮች ከአፍ እስከ ገደፍ እየመሉ ይገሰግሳሉ፤ ያን ጊዜ ዓባይ ከዳር ዳር በማዕበል ይሞላል፤ ያገኘውን ሁሉ እየጠረገ ይንጎማለላል፡፡ በዚህ ጊዜ ማዶ እና ማዶ የኾኑ የከንፈር ወዳጆች፣ ቅቤ ማሩን፣ ወርቅ አልማዙን በአጋሰስ የጫኑ ነጋዴዎች፣ ለጌታቸው መልእክት ሊያደርሱ በፈረስ የሚገሰግሱ ፈረሰኞች፣ በእግራቸው የሚፋጠኑ እግረኞች፣ በአሻገር ያለውን ዘመዳቸውን ለመጠየቅ የቋመጡ ወዳጅ ዘመዶች መሻገሪያ አጥተው ይጨነቃሉ፡፡

ነገሥታቱ፣ መኳንንቱ፣ መሳፍንቱ፣ ሀገረ ገዢዎች፣ የጦር አበጋዞች እና አሽከሮች ለመገናኘት ይቸገራሉ፤ ከወንዝ ማዶ እና ማዶ ኾነው በትዝታ ይኖራሉ፡፡ በዋና እንሻገራለን፣ በገመድም እናቋርጣልን፣ በታንኳ እንቀዝፋለን እያሉ እየገቡ በማዕበል ተጠልፈው የተወሰዱት፣ እንሻገራለን ብለው በወንዙ መካከል የቀሩት፣ ከእንጨት እና ከድንጋይ ጋር ተጋጭተው ለዘላለም ያሸለቡትም ብዙዎች ናቸው፡፡

ዓባይ ልጆቻቸውን በማዕበል እየጠለፈ የቀማቸው እናቶች እና አባቶች፣ የሚጠብቋቸውን በጎች እና ፍየሎች፣ ላሞች እና በሬዎች፣ ወይፈን እና ጊደሮች፣ ፈረስ እና በቅሎዎች እየነጠቀ የወሰደባቸው እረኞች፣ ወርቅ እና አልማዝ የጫኑባቸውን ግመሎች፣ የከበረ ማዕድን የያዙባቸውን ፈረስ እና በቅሎዎች፣ ሸጠው የሚያተርፉባቸውን ሃብቶች የነጠቃቸው ነጋዴዎች፣ የሚያጅቧቸው አሽከሮቻቸውን፣ እየተፋጠኑ የሚታዘዙላቸውን አገልጋዮቻቸውን የተነጠቁ ገዥዎችም ሞልተዋል፡፡ በሬውን ከእነቀንበሩ የነጠቃቸው ገበሬዎችም ብዙዎች ናቸው፡፡

ዘመንም ዘመንን እየተካ ሲሸጋገር ለዓባይ መሻገሪያ ይሰራ ዘንድ ግድ ኾነ፡፡ ያማሩ አብያተ መንግሥታትን፣ የተዋቡ አብያተ ክርስቲያናትን አሳምረው የሠሩት፣ ሀገራቸውን በሰላም ያረጉት፣ በሕዝባቸው ዘንድ አብዝተው የሚወደዱት፣ በጥበበኛ እጆቻቸው ለልጅ ልጅ የሚተርፍ የጥበብ አሻራ ያስቀመጡት፣ በጥበበኛ አዕምሯቸው ከትናንት ወዲያ ቆመው ዛሬን እና ነገን የተነበዩት፣ አሻግረውም የተመለከቱት ጥበበኛው ንጉሥ አጼ ፋሲለደስ ባማሩት አብያተ መንግሥታት አምሳል ዓባይን የሚያሻግር ድልድይ ሠሩ፡፡

ንጉሡ ዓባይን ደፍረው፣ ከጋራ እና ከጋራ ላይ ተክለው አሻግረዋልና አጀብ ተሰኙ፡፡ የሀገሬው ሰውም ንጉሡን አብዝቶ አደነቃቸው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ እርሳቸው ፋሲለደስ ሳይኾኑ አባታቸው አጼ ሱስንዮስ እንደሠሩት ይናገራሉ፡፡ ያም ኾነ ይህ ግን የመጀመሪያው የዓባይ ድልድይ ከአባት እና ልጁ አይዘለም፡፡

ዳሩ ከዓባይ እርዝመት፣ ከሚያደርሰው ከሀገሩ ስፋት አንጻር ይህ ድልድይ በቂ አልነበረም፡፡ ሌሎች ድልድዮችም ተሠሩ፡፡ በዓባይ ወንዝ ላይ ከተሠሩ ድልድዮች መካከል የባሕር ዳሩ የቀድሞው ድልድይ አንደኛ ነው፡፡ ይሄን ድልድይ ጣሊያን እንደሠራችው ይነገራል፡፡ በርከት ላሉ አስርት ዓመታት እግረኛ እና ፈረሰኛውን፣ በመኪና የሚሸጋገረውን ያሸጋገረው ይህ ድልድይ አንድ ለናቱ እየተባለ ሲጠራ ዓመታትን አሳልፏል፡፡ ስለ ምን ቢሉ አጋዥ የሚኾነው ተጨማሪ ድልድይ በከተማዋ አልነበረምና፡፡

ለዓመታት አያሌ ጫናዎችን የተሸከመው ድልድይ አጋዥ ድልድይ እንዲሠራለት ከተጠየቀ ዓመታት አልፈው ዓመታት ተተካክተዋል፡፡ አንድ ለእናቱ ድልድይ ብልሽት ሲገጥመው እንኳን ከጠረፍ ሀገር ወደ መሃል ሀገር የሚመጡት፣ ከመሃል ሀገር ወደ ጠረፍ የሚወጡት የረጅም ርቀት ተሸከርካሪዎች እና ተጓዦች ይቅርና ዓባይ ለሁለት የሚከፍላቸው የከተማዋ ነዋሪዎችም ለመገናኘት ይቸገራሉ፡፡

አንድ ለእናቱ ድልድይ እንደ ዐይን ሲሳሳለት የኖረ ነው፡፡ ድልድዩ አደጋ እንዳይገጥመው እና መሻገሪያ እንዳይጠፋ የሚጨነቁትም ብዙዎች ነበሩ፡፡ አሁን ሌላ ዘመን መጥቷል፤ አንድ ለእናቱ ድልድይ ዘመኑን የዋጀ፣ ከእርሱም የላቀ አጋዥ ድልድ አግኝቷል፡፡ ለባሕር ዳር ውበት ለግዮንም ሰገነት የሚኾን ዘመናዊ ድልድይ ተሠርቷልና፡፡

ከዓመታት በፊት የአዲሱ ድልድይ ግንባታ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ሲካሄድ በሰማይ ነፍሳቸውን ይማረውና የቀድሞው የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የነበሩት ሙሉቀን አየሁ ነባሩ የዓባይ ድልድይ እድሜ ጠገብ በመኾኑ፣ ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ፣ በየቀኑ ከሚያስተናግደው ተሸከርካሪ ክብደት አኳያ በመጎዳቱ፣ በየጊዜው ጥገና ቢደረግለትም፣ የጉዳቱ መጠን ከፍተኛ ስለኾነ ለእድሳትም ረጅም ጊዜ እየወሰደ፣ ኅብረተሰባችንን ለከፍተኛ እንግልትና እሮሮ በመዳረጉ አዲስ ድልድይ እንዲሠራ በየጊዜው በሚካሄዱ መድረኮች ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡

የከተማዋን ሕዝብ የዘመናት ተለዋጭ የዓባይ ድልድይ ጥያቄ ተቀብሎ የፌደራል መንግሥት ምለሽ በመስጠቱ እናመሰግናለን ብለው ነበር፡፡ አዲሱ ድልድይ ለሕዝብ ኩራት ከመኾኑ ባሻገር ኢትዮጵያን በድልድይ ሥራ አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርጋት ነው፤ አዲሱ ድልድይ ለባሕር ዳር ከጣና ሐይቅ እና ከዓባይ ወንዝ በተጨማሪ የክብር አክሊል ኾኖ እንድትደምቅ የሚያደርጋት ነውም ብለው ነበር፡፡

በወቅቱ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዳይሬክተር የነበሩት እና የአሁኑ የኢትዮጵያ ማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኘ ድልድዩ በኢትዮጵያ እስካሁን ከተገነቡት ድልድዮች ሁሉ የተለየ ነው ብለውታል፡፡ በአዲሱ ድልድይ አጀማመር የተገኙት ሁሉ የአዲስ ታሪክ ምስክር መኾናቸውንም ገልጸው ነበር፡፡ አዲሱ ድልድይም በዓባይ ድልድይ የተገነባ 10ኛው ድልድይ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የመጀመሪያው ድልድይ ከተገነባ ከ400 ዓመታት በኋላ የተገነባ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ከዓመታት በኋላ ዘመናዊ ድልድይ ለመገንባት ተረኛ ባለታሪክ በመኾናችን እጅግ እንኮራለን ብለውም ነበር፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ አዲሱ ድልድይ 380 ሜትር ርዝመት፣ 43 ሜትር የጎን ሥፋት አለው፡፡ ይኽም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ድልድይ ያደርገዋል፡፡

የሱዳንን ፖርት በመተማ በኩል ከመሀል ሀገር ጋር በማገናኘት ከጅቡቱ መንገድ ቀጥሎ ሁለተኛው የንግድ ወጪ እና ገቢ ኮርደር መኾኑንም አንስተው ነበር፡፡ በአፍሪካ ኅብረት በኩል ከ50 ዓመታት በላይ አፍሪካን በመንገድ የማገኛኘት ጥረት አካል ኾኖ ከግብጽ ካይሮ እስከ ደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን በመዘርጋት የሚገኘው ዋናው መንገድ አካል በመኾኑ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅምን ለኢትዮጵያ ለማስገኘት ዘመኑን የሚመጥን ድልድይ መገንባት ተገቢ ነው ነበር ያሉት፡፡

የከተማዋን ውበትም ይጨምራል፤ ከተማዋን ለብዙ ነገር ተመራጭ እንደሚያደርጋት እና ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ጉልህ አስተዋጽዖ እንደሚኖረውም አንስተዋል፡፡ የቀድሞዋ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን የሌሎች አፍሪካ ሀገራት የታሪክ፣ የስልጣኔ እና የባሕል መሠረት ዓባይ ወንዝ ላይ ሕዝብን ለበለጠ የእድገት ጎዳና የሚያንደረድር፣ አዲስ የታሪክ አሻራ ለመጣል የሚያስችለውን፣ በዓይነቱም ኾነ በዘመናዊነቱ ልዩ ኾኖ ድልድይ ማስጀመር ደስታው ልዩ ነው ብለው ነበር፡፡

በወቅቱ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የነበሩት እና የአሁኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ሁልጊዜ ስንጓጓለት የነበረው፣ ከዛሬ ነገ መቼ ትፈርሳለች እያለን እንደ ዐይናችን ብሌን የምንሳሳላት አንዷ ብርቅዬ ድልድያችን አሁን ሌላ ትልቅ እሴት፣ ሌላ ትልቅ ሃብት ፈጥራልናለችና እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡ ለባሕር ዳር ከተማ ትልቅ ጸጋ፣ ትልቅ እሴት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃብት ነው ብለው ነበር፡፡

የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ደግሞ ቀኑን ታሪካዊ ቀን ሲሉ ገለፁት፡፡ ባለፉት የለውጥ መንገዶች ከልካይ እና አግላይ የኾኑ ግንቦችን እያፈረስን ድልድይ እንሠራለን ብለናል፤ ድልድዩም በአብሮነት፣ በኢትዮጵያዊ አንድነት እና ኩራት አስተሳሰብ የሚገነባ ሁሉን አቀፍ የኾነ ነው፤ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ በውቢቷ ባሕር ዳር እንዲህ ዓይነት ድልድይ ማስጀመር ሃሳባችን፣ ራዕያችንን መሬት እያስነካን መኾኑን ማሳያ ነው ብለውታል፡፡

ድልድዩ ለባሕር ዳር ብቻ ሳይኾን ለኢትዮጵያውያን ኩራት፣ የሀገር ውስጥንም ኾነ የዓለም አቀፍ ግንኙነት የሚያስተሳስር፣ የሀገራችን ትንሳኤ እና የከፍታ ዘመን ማሳያ ስለኾነ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ደስ አለን ነው ያሉት፡፡ በዚህ ዘመን ባለ ታሪኮች ኾነን ዓባይን ከመነሻው እስከ መዳረሻው ለመግራት ጀምረናል፤ 10ኛውን ድልድይ በውቢቷ ከተማ ስናስጀምር ዓባይን የማልማት፣ ገናናነቱን የማሳደግ፣ የባሕር ዳርን እድገት ወደፊት የማራመድ ሂደት ስለኾነ፣ ጎበዝ ታሪክ እየሠራን ነው ነበር ያሉት፡፡

ለብዙ ገድል እና ታሪክ ሰላማችን ጠብቀን፣ አብሮነታችንን አጠናክረን፣ ዝቅ ከሚያደርጉን ስሜቶች ወጥተን፣ ታላቅነታችንን እውን የሚያደርግ ለበጠ ኩራት እና ሀገራዊ አቅም ታጥቀን መነሳት አለብን፤ ሁላችንም አንድ ኾነን ኢትዮጵያን እናሻግር፤ ዘመኑን ለብልጽግና እንጠቀምበት፣ የሚያዋጣን ለትውልድ የምናሻግረው ሃብት ነውና ለዚህ እንሰለፍ፤ ተያይዘን እንዝመት ሲሉም አሳስበው ነበር፡፡

አሁን ጅማሬው ተፈጽሟል፡፡ መሠረቱም ተቋጭቷል፡፡ ዓባይ ካማረ ውበት ላይ ውበት ጨምሯል፡፡ በኢትዮጵያ የተዋበው ድልድይ በውበት ታይቷልና፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የ50 ሚሊየን ብር ዕቅድን በማለፍ 120 ሚሊየን መግባት አለብን” የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀማል አህመድ
Next articleውዳሴ የምርመራ ማዕከል ለጽዱ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት 2 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርገ።