“ኀብረተሰቡ ለጽዱ ኢትዮጵያ ከሚያበረክተው ገንዘብ ላይ አንድ ሦስተኛውን ጨምሬ አስገባለሁ” የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

28

ባሕር ዳር: ግንቦት 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኅብረተሰቡ ለጽዱ ኢትዮጵያ ከሚያበረክተው ገንዘብ ላይ አንድ ሦስተኛውን ጨምሮ እንደሚያስገባ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታውቋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ እንደገለጹት የጽዱ ኢትዮዽያ ፕሮጀክት ጉዳይ ከገንዘብ ያለፈ ትርጉም ያለው በመኾኑ ንግድ ባንኩ እያንዳንዱ ዜጋ ከሚያደርገው ድጋፍ ላይ አንድ ሦስተኛውን ጨምሮ ያስገባል ብለዋል።

አንድ ዜጋ ሦስት ብር ሲያስገባ ባንኩ አንድ ብር ይጨምራል ነው ያሉት። ለምሳሌ 30 ሚሊየን ብር ቢሰበሰብ ባንኩ 10 ሚሊየን ብር ጨምሮ 40 ሚሊዮን ብር አድረጎ ያስገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ እንደተናገሩት ኅብረተሰቡ ያበረከተው ገንዘብ ገቢ መኾኑን የሚያረጋግጥበት አሠራርም ተዘጋጅቷል። ንግድ ባንክ ለሀገራዊ ጉዳይ ምንጊዜም ዝግጁ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ይህ ቴሌቶን እንዲሳካ መላ ሠራተኞች ዝግጁ ኾነው በሥራ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

የቴሌቶኑ ገቢ አሰባሰብ ሂደቱን በቀጥታ ማስተላለፍ ከተፈለገም በዚያ ልክ ተዘጋጅተናል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ። ኢትዮጵያን በተመለከተ ጉዳይ ባንካቸው ቀዳሚ መኾን እንደሚፈልግ የገለጹት ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ በግላቸውም ለጽዳት ፕሮጀክቱ ለሦስተኛ ጊዜ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
ጽዳት ሰብዓዊነትን የሚያስከብር በመኾኑም ለፕሮጀክቱ ድጋፍ የማድረግን ተገቢነት አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበ1 ሰዓት ውስጥ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ተሰበሰበ።
Next article“ውኃ እንደ ቁምነገር ሰውን ካስከበረ፤ ዓባይ እና ጣና ሀገሬ ነበረ”