
ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ባደረገችው ሥምምነት መሠረት ግንቦት 3 ቀን 1956 ዓ.ም የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ተቋም ተመሠረተ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፤ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ይሄዳሉ፡፡ የሶቭየት መሪዎችም ንጉሡ ሀገራቸውን ስለጐበኙላቸው ለንጉሣዊው ክብር ምላሽ በማሰብ በጀት መድበው በባሕር ዳር ከተማ የፖሊ ቴክኒክ (ተቋም) ኢንስቲትዩት እንዲቋቋም ሥምምነት ላይ ተደረሰ፡፡
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም በዚሁ ዓመት ተቋሙን ለመገንባት የሚያስችል የመሠረት ድንጋይ ባስቀመጡበት እና ግንባታውን ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት በሀገራችን ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት እና ወደ ዘመናዊነት ለመሸጋገር የተቋሙ መቋቋም ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ማለታቸው ተዘግቧል፡፡ የባሕር ዳር የፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት ሲመሠረትም እስከ አንድ ሺህ ሠልጣኞችን እንዲቀበል ታሳቢ ተደርጎ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ድረ ገጽ እንዳሰፈረው ኢንስቲትዩቱ ሥራውን ሲጀምርም “የፖሊ ቴክኒክ ትምህርት ቤት” ይባል ነበር፡፡ አንድ ተማሪ ወደ ተቁሙ ለመግባት ቢፈልግ በተቋሙ የሚሰጠውን የመግቢያ ፈተና ማለፍ ግዴታው ነበር፡፡ የባሕር ዳር የፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት በወቅቱ ሥልጠና የሚሰጠው በአምስት የቴክኖሎጂ ትምህርት ዓይነቶች ነበር፡፡ ማለትም:- በአግሮ ሜካኒክስ፣ በኤሌክትሪካል ምህንድስና፣ በቴክስታይል ቴክኖሎጂ፣ በኢንድስትሪያል ኬሚስትሪ እና በእንጨት ቴክኖሎጂ ነበር፡፡
ተቋሙ ማስተማር በጀመረ በስድስተኛ ዓመቱ በ1962 ዓ.ም የብረታብረት ቴክኖሎጂ ስድስተኛውን የትምህርት ዘርፍ ከፈተ፡፡ ለኢንስቲትዩቱ የትምህርት መስኮች የሶቭየት ኅብረት መንግሥት የትምህርት ቁሳቁስ ያሟላ ሲኾን ሥርዓተ ትምህርትም በመቅረፅ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል፡፡ ተቋሙ ማሥተማር የጀመረው በ20 ኢትዮጵያውያን፣ በ19 ሩሲያውያን እና በዘጠኝ ሕንዳውያን በአጠቃላይ በ48 መምህራን እና በ40 የአሥተዳደር ሠራተኞች ነበር፡፡
የባሕር ዳር የፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት ለመጀመሪያ ጊዜ 237 ሠልጣኞችን ተቀብሎ ሥልጠናውን የጀመረ ሲኾን ሥልጠናውን አጠናቅቀው የተመረቁት 150 ሠልጣኞች ብቻ ነበሩ፡፡ ኢንስቲትዩቱ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮም አዳዲስ የትምህርት መስኮችን በመክፈት ሥልጠናውን በዲግሪ ደረጃ አሳድጓል፡፡
👉 የቀይ መስቀል “አባት”
ሄነሪ ዱና የቀይ መስቀል መሥራች ናቸው፡፡ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ቀን በየዓመቱ ሚያዝያ 30 ሲታዎስ እሳቸውም ይዘከራሉ፡፡ ሄነሪ ዱና ቀይ መስቀልን ለመመስረት መነሻ የኾናቸው ፈረንሳይ እና ጣሊያን በአንድ ወገን ኾነው ከኦስትሪያ ጋር በሳልፋሪኖ ጦርነት ተተጋትገዋል፤ በጦርነቱም 40ሺህ ሰዎች ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡
በዚህ አሰቃቂ ዕልቂት ወቅት ሄነሪ ዱና የንግድ ሥራቸውን ትተው ሰላማዊ ሰዎችን በማስተባበር የቆሰሉትን አሳከሙ፤ የሞቱትን ቀበሩ፤ ከቤተሰቦቻቸው የተጠፋፉትን አገናኙ፡፡ “የሳልፋሪኖ ማስታወሻ” በሚልም መጽሐፍ ጽፈው ለንባብ አብቅተዋል፡፡ ከመጽሐፉ መታተም በኋላ በጦርነት ወቅት ቁስለኞችን በገለልተኝነት የሚረዳ ተቋም እንዲመሰረትም ሀሳብ ቀረበ፡፡ የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበርም የተመሰረተው እሳቸው “የሳልፋሪኖ ማስታወሻ” በመጻፋቸው ነው፡፡ ስለኾነም እ.አ.አ ሚያዝያ 30 ቀን 1864 በ12 ሀገራት ጄኔቫ ላይ ቀይ መስቀል መመስረቱን ይፋ የኾነበት ስምምነት ተፈረመ።
በመኾኑም ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ቀን በየዓመቱ ሚያዝያ 30 ይታወሳል በማለት ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡ ኢትዮጵያም በፓሪስ የኢትዮጵያ አምባሳደር በነበሩት በጅሮንድ ተክለሀዋርያት አማካኝነት ሐምሌ 18 ቀን 1927 ዓ.ም የጀኔቫ ስምምነቶችን በመፈረም ከዓለም 48ኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ እና ግብጽ በመቀጠል 3ኛ ሀገር በመኾን ቀይ መስቀልን አቋቁማለች።
የሂሮሺማ እና ናጋሳኪ የአቶሚክ ቦምቦች አስተኳሽ ሃሪ ኤስ.ትሩማን ይባላሉ፡፡ የፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ሞትን ተከትሎ 33ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ነበሩ፡፡ የትሩማን ቤተሰብ ልጃቸውን ወደ ኮሌጅ የመላክ አቅም ስላልነበራቸው በ1901 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንደጨረሰ የእርሻ ሥራ አከናውነዋል፡፡ በመቀጠልም የባንክ ጸሐፊ ኾነው ሠርተዋል፡፡በተጨማሪም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሀገራቸውን በሚዙሪ ብሔራዊ ጥበቃ ውስጥም በወታደርነት አገልግለዋል።
እ.ኤ.አ. በ 1917 አሜሪካ ወደ አንደኛው የዓለም ጦርነት ስትገባ ትሩማን በብሔራዊ ጥበቃ ውስጥ እንደገና ተመዝግበው ወደ ፈረንሳይ ተልከው የመድፍ ክፍል ካፒቴን ኾነው የዜግነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1919 ከጦርነቱ ከተመለሱ በኋላ የልጅነት የትምህርት ቤት ጓደኛቸውን ኤልዛቤትን አግብተው ዐይናቸውን በዐይናቸው አይተዋል፡፡
ሃሪ ኤስ.ትሩማን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እና በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በአውሮፓ የሶቪየትን መስፋፋት አጥብቀው በመቃወማቸው በአሜሪካ ሕዝብ ዘንድ ብሔራዊ ጀግና አስብሏቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ትሩማን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጃፓኖችን ትላልቅ ከተሞች ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ በአቶሚክ ቦምብ እንዲደበደቡ ትእዛዝ የሰጡ ፕሬዚዳንት ናቸው።
አሜሪካም በዓለም ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአቶሚክ ቦምብ የጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ ያዋለችበት ጊዜም ነበር። እኝህ ፕሬዚዳንት የተወለዱት ግንቦት 8 ቀን 1884 በዚህ ሳምንት ነው፤ ለተጨማሪ መረጃ ትሩማን ላይበራሪዶትጅኦቪን ይጎብኙ፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!