የውጭ ባለሃብቶች በተመረጡ የንግድ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ መፈቀዱ የሥራ እድልን ለማሥፋት ያግዛል ተባለ።

24

ባሕር ዳር: ግንቦት 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ለዜጎች ብቻ ተከልሎ የነበረው የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላ እና የችርቻሮ ንግድ ላይ የውጭ ባለሃብቶች እንዲሳተፉበት የሚፈቅድ አዲስ የአፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 1001/2016 መጽደቁ ይታወሳል።

በመመሪያው መሠረት የውጭ ባለሃብቶች ቅድመ ሁኔታዎችን እስካሟሉ ድረስ በጥሬ ቡና፣ በቅባት እህሎች፣ በጫት፣ በጥራጥሬ፣ በቆዳና ሌጦ፣ የደን ውጤቶች፣ የዶሮ እና የቁም እንስሳት የወጪ ንግድ ገበያ ላይ መሳተፍ ይችላሉ።

ከማዳበሪያ እና ነዳጅ በስተቀር በሁሉም የገቢ ንግድ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይም መሳተፍ እንደሚችሉም በመመሪያው ተጠቅሷል።

በኤክስፖርት እና ተኪ ምርቶች ላይ የተሰማሩ ድርጅት ኀላፊዎች እንዳሉት ይኸ መመሪያ ፍትሃዊ የንግድ ውድድር በመፍጠር ሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያላቸውን ምርቶችን እንዲያገኙ ያግዛል።

የአላና ግሩፕ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ከሊፋ ሁሴን እንዳሉት ድርጅታቸው ከሕንድ ወደ 78 ሀገራት ሥጋ በመላክ ሥራ ላይ ተሰማርቷል፡፡ በኢትዮጵያም 100 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ያደረገ እና ሁለት ዘመናዊ የኤክስፖርት ቄራዎች እንዳሉት ተናግረዋል። ዋና ሥራ አስኪያጅ ከሊፋ ሁሴን መመሪያው ለፍትሃዊ የንግድ ውድድር እና ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚያስችል ነው።

የሞሃን ግሩፕ ፒኤልሲ ሥራ አስኪያጅ ሀርሽ ኮታሪ በበኩላቸው ድርጅታቸው ለጫማ፣ ወንበር፣ ለማሸጊያ፣ ለኤሌክትሪክ ኬብል ማምረቻ የሚያገለግል ፖሊመር የተሰኘ ጥሬ እቃ እንዲሁም የተለያዩ ጫማዎችን ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ መኾኑን ይገልጻሉ።
መመሪያው አቅም ያላቸው ዓለም አቀፍ የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ በማበረታታት የእውቀት፣ ክህሎት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ይፈጥራል ብለዋል።

መመሪያው የሀገር ውስጥ ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ ተቀባይነት እንዲያገኝ በማስቻል የኢኮኖሚ እድገቱን ለማሣለጥ የሚያግዝ መኾኑንም ባለሃብቶቹ ተናግረዋል። የሥራ እድልን ለማሥፋት እና ምርቶች በተሻለ ዋጋ እና ጥራት ለሸማቹ እንዲቀርቡ መንገድ የሚከፍት መኾኑንም አሥረድተዋል።

መመሪያው የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ከውጭ ባለሃብቶች ጋር ለመወዳደር የሚያስችላቸውን ዘመናዊ የአሠራር ዘዴዎች እንዲከተሉ እንደሚያነሳሳቸው አቶ ከሊፋ ተናግረዋል።

የሞሃን ግሩፕ ፒኤልሲ ሥራ አስኪያጅ ሀርሽ ኮታሪ በበኩላቸው የሀገር ውስጥ ነጋዴዎች ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ለመወዳደር ብቃታቸውን ማጎልበት ላይ አተኩረው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

መንግስት ቀልጣፋ ፍትሕዊ እና ከሙስና የጸዳ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር እና በንግድ ስም ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት ለማጭበርበር የሚጥሩ አካላት ላይ ቁጥጥር ማድረግ አለበት ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበኢትዮጵያ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር እና የፋይናንስ ዘርፉ እንዲያድግ እየተሠራ መኾኑን የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።
Next articleበአማራ ክልል በፍትሕ ዘርፉ ያሉ መመሪያዎችን እና አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ለዜጎች ፈጣን አገልግሎት እየተሰጠ መኾኑ ተገለጸ።