
አዲስ አበባ: ግንቦት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር እና የፋይናንስ ዘርፉ እንዲያድግ እየተሠራ መኾኑን የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህርቱ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የኢንቨስትመንት እና የግሉ ዘርፍ የቢዝነስ ኹኔታ ምቹ እንዲኾን በሚያስችሉ መፍትሔዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።
ውይይቱ እየተካሄደ ያለው በኢትዮጵያ ታምርት የ2016 ኤክስፖ ሦስተኛ ቀን መርሐ ግብር ላይ ነው፡፡ ውይይቱ “የግል ኢንቨስትመንት እና አስቻይ ኹኔታዎች” በሚል መሪ መልዕክት ነው የሚካሄደው፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥው ትናንሽ ኢንተርፕራይዞች ብድር የሚወስዱበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ ስለመኸኑ በውይይቱ ላይ ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ዓመት 33 ነጥብ 5 የነበረውን የዋጋ ግሽበት በዘንድሮው ዓመት 23 ነጥብ 3 የደረሰ ሲኾን፤ በ10 ነጥብ 2 ቀንሷል ብለዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ፣ የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኝ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ፣ የኢትዮጽያ ኤሌክትርክ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ.ር)፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!