“በኮሪያ ሰላም ማስከበር የተሰማራው የቃኘው ሻለቃ ጦር የፈጸመው ገድል ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው” አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ

22

ባሕር ዳር: ግንቦት 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኮሪያ ሰላም ማስከበር የተሰማራው የቃኘው ሻለቃ ጦር የፈጸመው ገድል ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ መኾኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ማኅበር ኢትዮጵያ ሰላም ለማስከበር ወደ ኮርያ የዘመተችበትን 73ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲያከብር ነው።

አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በኮርያ ሰላም ማስከበር ላይ ለተሳተፉ ዘማቾች ክብር መስጠት እና ማመስገን ብሎም ታሪካቸውን መሰነድ ይኖርብናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለኮርያ ሰላም መረጋገጥ ያበረከተችው አስተዋጽኦ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ያጠናከረ እንደኾነም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በወቅቱ ያበረከተችው አስተዋጽኦ የሀገራችንን ሕዝቦች በጎነት ያሳየ መኾኑን አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ የደቡብ ኮርያ አምባሳደር ጃንግ ካንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለኮሪያ ሰላም የከፈለችው ዋጋ የማይዘነጋ መኾኑን ገልጸዋል፤ ለዚህም አመስግነዋል።

የተከፈለው ዋጋ በኢትዮጵያ እና በኮርያ መካካል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲጠናከር መሠረት መጣሉንም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት ኮሎኔል እስጢፋኖስ ገብረመስቀል በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ወደ ኮሪያ የዘመቱበትን 73ኛ ዓመት በተለያዩ መርሐ ግብሮች ማክበራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ፣ በኢትዮጵያ የደቡብ ኮርያ አምባሳደር ጃንግ ካንግ፣ የኮርያ ዘማች ቤተሰቦች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሠራ መኾኑን የጤና ሚንስቴር አስታወቀ፡፡
Next articleበኢትዮጵያ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር እና የፋይናንስ ዘርፉ እንዲያድግ እየተሠራ መኾኑን የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።