በጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሠራ መኾኑን የጤና ሚንስቴር አስታወቀ፡፡

38

ባሕር ዳር: ግንቦት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ መዋጮን በአግባቡ መሰብሰብ እና የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን የማስፋፋት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ መኾኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የጤና መድህን አገልግሎት ዜጎች ብዙ ወጪ ሳያወጡ ጤናቸውን እንዲጠብቁ ምቹ እድልን እየፈጠረ ሲኾን ሕክምና ባለማግኘት የሚያጋጥም ዘላቂ የጤና ችግርን ለመግታትም ዓይነተኛ ሚናን እየተወጣ መኾኑ ተጠቁሟል፡፡

የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመላክተው ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ዱጉማ (ዶ.ር) የጤና መድህን አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ቢከናወኑም አሁንም በኅብረተሰቡ ዘንድ በአገልግሎት አሰጣጥ እና በአቅርቦት ማነስ ምክንያት ቅሬታ እየቀረበ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መዋጮን በአግባቡ መሰብሰብ እና የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን ማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል። በተለይም የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤቶች በሁሉም ወረዳዎች እንዲከፈቱ ማድረግ እና በተለየ ተነሳሽነት የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎችን ማበራከት ላይ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የአባላትን ቁጥር የመጨመር ሥራ በሚጠበቀው ልክ አለመሠራቱ፤ እንዲሁም ከማኅበረሰቡ የሚሰበሰበው ገንዘብ በጊዜ ወደ ባንክ አለመግባቱ ሌላው ችግር መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም የጤና መድህን አገልግሎት የሚመራበትን የአሠራር ማዕቀፍ በማዘጋጀት በሁሉም ደረጃ ያሉ አመራሮች ቀዳሚ ሥራ እንዲኾን በጤና ሚኒስቴር በኩል ክትትል እየተደረገ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡

ከጤና መድህን አባላት የሚሰበሰበው ገንዘብም ከተሰበሰበ በኋላ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ወደ ባንክ ገቢ እንዲደረግ አቅጣጫ መቀመጡንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ለክልል ጤና ኬላዎች እና ጤና ጣቢያዎች የሕክምና መሳሪያዎች እና ተሽከርካሪ ማሟላት፣ ጽሕፈት ቤቶችን ማደራጀት እና ምቹ የጤና አገልግሎት መስጫ አካባቢን በመፍጠር በኩልም ድጋፍ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ቅሬታን ለመፍታት ያግዛሉ ተብለው በቀጣይ ከተያዙ እቅዶች አንዱ ለጤና ባለሙያዎቹ ምቹ የሥራ አካባቢን የመፍጠር ሥራ እንደሚከናወንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ወርቁ የአገልግሎቱን ጠቀሜታ የማስረዳት ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህ ወቅት በሀገሪቷ በሚገኙ ከ3 ሺህ 630 በላይ የጤና ተቋማት የጤና መድህን አገልግሎት እየተሰጠ መኾኑን ጠቁመው በሕዝብ አቅም በተገነቡ 472 ሞዴል የማኅበረሰብ መድኃኒት ቤቶችም በተመጣጣኝ ዋጋ መድኃኒት እየቀረበ መኾኑንም ተናግረዋል።

የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ አባላትን ቁጥር ለመጨመር ከተሞችን፤ የመንግሥት ተቋማት እና ጡረተኞችን የማሳተፍ ጥረት እየተደረገ መኾኑን አስረድተዋል።

በቀጣይ የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት በአርብቶ አደር እና በከፊል አርብቶ አደር ወረዳዎች አገልግሎቱ እንዲጀመር አስፈላጊ ድጋፎች ይደረጋሉ ብለዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለ2016/17 የምርት ዘመን የማዳበሪያ ግዢ እና ሥርጭት በተሻለ መንገድ እየተፈጸመ መኾኑ ተገለጸ።
Next article“በኮሪያ ሰላም ማስከበር የተሰማራው የቃኘው ሻለቃ ጦር የፈጸመው ገድል ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው” አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ