ለ2016/17 የምርት ዘመን የማዳበሪያ ግዢ እና ሥርጭት በተሻለ መንገድ እየተፈጸመ መኾኑ ተገለጸ።

20

ባሕር ዳር: ግንቦት 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለ2016/17 የምርት ዘመን 19 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ ለመግዛት አቅዶ ግዥ እየፈጸመ ይገኛል።

መንግሥት ለማዳበሪያ ግዥው 930 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በጀት መድቧል።

ከተገዛው ማዳበሪያ ውስጥ እስከ ግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ 12 ሚሊየን 729 ሺህ 69 ኩንታል ማዳበሪያ በ29 መርከቦች ከውጭ ተጓጉዞ ጂቡቲ ወደብ ደርሷል።

ወደብ ከደረሰው ማዳበሪያ ውስጥ ደግሞ 11 ሚሊየን 581 ሺህ 542 ኩንታል ወይም 91 በመቶ የሚኾነው በከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች እና በባቡር ትራንስፖርት ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ በመሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሮች እየቀረበ ነው።

ኮርፖሬሽኑ ባለፈው የምርት ዘመን 2015/16 ከውጭ የገዛው የአፈር ማዳበሪያ መጠን 13 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል ነበር። ለ2016/17 የሚገዛው የማዳበሪያ መጠን ካለፈው የምርት ዘመን ማዳበሪያ ጋር ሲነጻጸር የ5 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ አለው።

የአፈር ማዳበሪያ ግዥ የተፈጸመው መስከረም 2016 ዓ.ም ሲኾን የመጀመሪያዋ መርከብ ጥቅምት 2016 ዓ.ም ጁቡቲ ወደብ ደርሳለች። ሥርጭቱም ከጥቅምት ወር አንስቶ ተጀምሯል።

ባለፈው ዓመት የአፈር ማዳበሪያ ግዥ የተፈጸመው ጥቅምት 2015 ዓ.ም ሲኾን የመጀመሪያዋ መርከብ ጁቡቲ የደረሰችው ታህሳስ 2015 ዓ.ም ነበር። ሥርጭቱም በታህሳስ ወር ነበር የተጀመረው።

የግብርና ሚኒስቴር በየዓመቱ እያጠና በሚያቀርበው የሀገሪቱ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት መሠረት የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከተቋቋመበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ዓለም አቀፍ ጨረታ እያወጣ የማዳበሪያ ግዥ በመፈጸም ላይ ይገኛል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ ነዳጅ ማደያዎች ላይ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል አዋጅ መዘጋጀቱን የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታወቀ።
Next articleበጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሠራ መኾኑን የጤና ሚንስቴር አስታወቀ፡፡