የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ ነዳጅ ማደያዎች ላይ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል አዋጅ መዘጋጀቱን የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታወቀ።

17

ባሕር ዳር: ግንቦት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሰሃረላ አብዱላሂ በኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ከማሸግ የዘለለ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሕጋዊ አሠራር አለመኖሩን ገልጸዋል።

ከችግሩ አሳሳቢነት አኳያም ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ማደያዎቹን ከማሸግ ያለፈ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችል አዋጅ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

በአዋጁ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሰው ሰራሽ የነዳጅ እጥረት በሚፈጥሩ ሕገ ወጦች ላይ እስራት እና የገንዘብ ቅጣት እርምጃ መውሰድ የሚያስችሉ አንቀጾች መካተታቸውን ጠቁመዋል።

በአዋጁ ላይ ከነዳጅ ኩባንያዎች፣ከፈሳሽ ጭነት አሽከርካሪ ማኅበራት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ግብዓት መሠብሠብ መቻሉን ነው የገለጹት።

አዋጁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን ተከትሎ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ባለሥልጣኑ በዘርፉ ያለውን ሕገ-ወጥነት ለመከላከል ከአምስት ወር በፊት አዳዲስ የነዳጅ ማደያ ፈቃድ እንዳይሰጥ ክልከላ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ክልከላው የተደረገው ለነዳጅ ማደያ ግንባታ ራሱን የቻለ ደረጃ እና መስፈርት ባለመውጣቱ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ባለሥልጣኑ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢኒስቲትዩት ጋር በመሆን ለነዳጅ ማደያ ግንባታ የሚያስፈልግ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የጥራት መስፈርት ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእየተወሰደ ያለው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።
Next articleለ2016/17 የምርት ዘመን የማዳበሪያ ግዢ እና ሥርጭት በተሻለ መንገድ እየተፈጸመ መኾኑ ተገለጸ።