
ባሕር ዳር: ግንቦት 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኮማንድፖስቱ እየተተገበረ ያለው የሕግ ማስከበር ተግባር በዜጎች ላይ የመብት ጥሰት እንዳይደርስ በጥንቃቄ መተግበሩ በሕዝቡ ቅቡልነት እንዲኖረው ማድረጉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ ገልጿል፡፡
መርማሪ ቦርዱ የሕግ ማስከበር ሥራው በአካባቢው ያለው ሰላም እያደገ እንዲሄድ ሚናው የጎላ መኾኑንም አመላክቷል።
የቦርዱ አባላት በአማራ ክልል በሰሜን ምዕራብ ኮማንድፖስት ሥር በጎንደር ከተማ በሚገኘው ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ ተገኝተው ምልከታ አድርገዋል፡፡
በምልከታውም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የተያዙ ተጠርጣሪዎች በምህረት እና የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ መደበኛ ሥራዎቻቸው እንዲመለሱ በመደረጉ የተጠርጣሪዎቹ ቁጥር በእጅጉ እንደቀነሰ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ቀስ በቀስ እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ አሁን ላይ ከኅብረተሰቡ ጋር በመኾን የተለያዩ መደበኛ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም የኮማድፓስቱ የሥራ ኀላፊዎች ለቦርዱ አባላት ገልጸዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሰፈረው በክልሉ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት በማረጋገጥ ትኩረትን ወደ ልማት ማዞር ይገባል ሲል መርማሪ ቦርዱ መግለጹን አስታውቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!