ዘርን ከታወቀ ምርጥ ዘር አቅራቢ በመግዛት ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

25

ባሕር ዳር: ግንቦት 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደር አማኑኤል ታደገ ይባላሉ፡፡ የጃቢ ጠህናን ወረዳ ነዋሪ ናቸው። ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን እውቅና የሠጠውን የበቆሎ ምርጥ ዘር በመግዛታቸው ምርታቸው መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደር አማኑኤል በ2015/16 የመኸር እርሻ የተጠቀሙበት የበቆሎ ምርጥ ዘር ሁለት ዓይነት ነበር፡፡ ያገኙት ምርትም የተለያየ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ የማሳ ስፋት የዘሩት የበቆሎ ሰብል በሰባት ኩንታል እንደተበላለጠ ይናገራሉ፡፡

አርሶ አደር አማኑኤል ዘር ሲገዙ እንዳይጭበረበሩ ብርቱ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ በዘሩ ላይ የተለጠፉ መለያ ጽሑፎችን በማንበብም እንደሚገዙ ነግረውናል፡፡ “አንድ ክረምት የነቀለውን 10 ክረምት አይተክለውም” ነውና ነገሩ ዘር ሲገዛ መጠንቀቅ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ በዘሩ ላይ ሁለት ወረቀቶች መለጠፋቸውንም አረጋግጠው እንደሚገዙ ተናግረዋል፡፡

ዘሩ ሲከፈትም ከውስጥ ወረቀት ይገኛል ይላሉ፡፡ የተሻለ ውጤት በማግኘታቸው ባለፈው ዓመት የተጠቀሙበትን እና የክልል መንግሥት ምርታማነቱ እና ለአካባቢው ሥነ ምህዳር ተስማሚ ነው ያለውን ዘር ዘንድሮም ገዝተዋል፡፡ ለሌሎች አርሶ አደሮችም ዘር ሲገዙ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

የበቆሎ ዘር አቅራቢ ድርጅት ወኪል አከፋፋይ የኾኑት ድረስ ዓለማየሁ ናቸው፡፡ እውቅና የተሠጠውን ዘር ተረክበው እንደሚያሠራጩ ነግረውናል፡፡ ወኪል አከፋፋይ በመኾናቸው ከእሳቸው የሚጠበቀውን ደረጃውን የጠበቀ መጋዝን አዘጋጅተውም እንደሚረከቡ ነው የነገሩን፡፡

የሚረከቡት ዘር ሁለት መለያ ጽሑፍ የተለጠፈበት እንደኾነም ነው የሚናገሩት፡፡ በወረቀቶቹ ላይ የዘሩ የጥራት ሁኔታ፣ የዘሩ የብቅለት መጠን፣ ዘሩ መቼ እንደታሸገ እና መሠል ነገሮች ይጻፉበታል ነው ያሉት፡፡ አርሶ አደሮች ምርጥ ዘር ሲገዙ ሕጋዊውን ቦታ አውቀው ማንበብ እንኳን ባይችሉ ለሌሎች ሰዎች በማስነበብ ትክክለኛው ዘር መግዛት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን የዘር ጥራት ቁጥጥር ባለሙያ ሰለሞን ሺገድብ ለ2016/17 ለመኸር እርሻ ጥቅም ላይ የሚውል በክልሉ አቅም ዘር ሲባዛ መቆየቱን አንስተዋል።

በክልሉ በርካታ ዘር የተሰበሰበ ሲኾን የማጥራት እና በኬሚካል የማሸት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የተዘጋጀውን ዘር የጥራት ቁጥጥር የማድረግ ሥራ የዝግጅቱ አካል መኾኑንም ተናግረዋል። በመስክ የጥራት ቁጥጥር ተደርጎበት የተሰበሰበውን ዘር የኢትዮጵያ የዘር ደረጃ መስፈርትን ማሟላት አለማሟላቱን ማረጋገጥ ሌላኛው የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሥራ ነው ብለዋል። በመስክ ጉብኝት ጥራቱ የተረጋገጠው ዘር በቤተ ሙከራ ጥራቱ ተረጋግጦ ለአርሶ አደርች ለማቅረብ ይሠራል ብለዋል፡፡

በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በብዛት የሚዘጋጁ እና የጥራት ቁጥጥር የሚደረግባቸው የሰብል ዓይነቶች በቆሎ፣ ሥንዴ፣ የቢራ ገብስ፣ ማሽላ፣ ጤፍ እና አኩሪ አተር እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡

የዘር ዓይነቶች እንደሚዘሩበት ወቅት በቅደም ተከተል ተዘጋጅተው ለአርሶ አደሮች እንደሚቀርቡም ተናግረዋል፡፡ የዘር ዓይነቶቹ እንደሚዘሩበት ሥነ ምህዳር የተለያዩ እንደኾኑም ነው የተናገሩት፡፡ ለምሳሌ በቆሎ ለደጋው፣ ለወይናደጋው እና ለቆላው ተብሎ ተለይቶ እንደሚዘጋጅ ያነሱት ባለሙያው አርሶ አደሮች ለአካባቢያቸው ተብሎ የተዘጋጀውን ዘር መግዛት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

አቶ ሰለሞን አርሶ አደሮች ለአካባቢው ሥነ ምህዳር የሚስማማውን ዘር በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በ2003 እና በ2004 ዓ.ም የነበረውን የዘር አቅርቦት እጥረት እና የስርጭት ችግር ለመከላከል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አንድ ዘር ጥራቱን ጠብቆ መዘጋጀቱን እና ለሚፈለገው አካል መድረሱን ማረጋገጥ እንዲኹም የዝርያ ጥራት፣ አካላዊ ጥራት እና የዘሩን ጤና ማረጋገጥ ዋናው ሥራው መኾኑንም ነው የገለጹት፡፡

ባለሙያው የዘር ግብይት በሁለት መንገድ እንደሚፈጸምም ተናግረዋል፡፡ አንደኛው በዩኔኖች ወይም ዘር እንዲያመርቱ በተቋቋሙ ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ሲኾን ሌላው ደግሞ ዘር እንዲያመርቱ የብቃት ማረጋገጫ በተሠጣቸው ዘር አቅራቢዎች እና እነሱ ዘር እንዲያሰራጩ ውክልና በሠጧቸው አካላት እና ወኪሎቻቸው አማካኝነት መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡

አርሶ አደሮች በተለይ የበቆሎ ምርጥ ዘር ሲገዙ በክልሉ መንግሥት ዘር እንዲያቀርቡ ኀላፊነት ከተሰጣቸው አካላት መግዛት እንደለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

አርሶ አደሮች ምርጥ ዘር ሲገዙ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እና የዘር አምራች ድርጅቱ መለያ ጽሑፍ የተለጠፈበትን ለይተው መግዛት አለባቸው ብለዋል፡፡ የዘር አምራች ድርጅቱ መለያ ጽሑፍ ሥለዘሩ አጠቃላይ መረጃ የያዘ ሲኾን፣ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መለያ ጽሑፍ ደግሞ የጥራት ቁጥጥር የተደረገበት ዘር መኾኑን የሚገልጽ ነው ብለዋል፡፡ መለያ ጽሑፍ በሌሎች አካላት ተመሳስሎ እንዳይሠራ ለእያንዳንዱ ዘር ባር ኮድ ወይም ሚስጥራዊ መለያ የተሠጠው ኾኖ መሠራቱንም ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮች ዘሩን ገዝተው ዘርተው ችግር ቢያጋጥማቸው ዘር የሸጠላቸውን አካል ካሳ የመጠየቅ እድል እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡ ይኽም የሚኾነው አርሶ አደሮች ዘሩ ላይ የተለጠፈውን ሁለት መለያ ጽሑፍ እና ዘሩ ሲከፈት የሚገኘውን መለያ ጽሑፍ ሰብሉ እስኪሰበሰብ በጥንቃቄ ማስቀመጥ ከቻሉ እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡ እንዲኹም ዘር ሲገዙ የሸጠላቸውን አካል ስማቸውን፣ የሚኖሩበትን አካባቢ እና የወሰዱትን የዘር መጠን በትክክል እንደመዘገበላቸው እርግጠኛ ሲኾኑ ብቻ ነው ብለዋል፡፡

አርሶ አደሮች ዘርን ከታወቀ ምርጥ ዘር አቅራቢ ድርጅት በመግዛት ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በአሜሪካ እየተካሄደ በሚገኘው የሮቦፌስት ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡
Next articleየመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ያሥገነባቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለባለ ዕድለኞች በእጣ ሊያስተላልፍ ነው፡፡