ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በአሜሪካ እየተካሄደ በሚገኘው የሮቦፌስት ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡

15

ባሕር ዳር: ግንቦት 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በዓለም አቀፍ የሮቦፌስት ውድድር ለመሳተፍ ወደ አሜሪካ አቅንተው በውድድሩ ላይ እየተሳተፉ ነው። ተወዳዳሪዎቹ ወደ ዓለም አቀፉ መድረክ ያመሩት በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ድጋፍ፣ አብርሆት ላይብራሪ ከአቦጊዳ የሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ ማዕከል ጋር በመተባበር ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችን በዓለም አቀፍ መድረኮች ለማወዳደር በገቡት ስምምነት መሰረት መኾኑም ተገልጿል።

አሜሪካ በሚገኘው የሚችጋን ላውረንስ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በሚካሄደው ውድድር 23 ታዳጊዎች ኢትዮጵያን ወክለው በተለያዩ ዘርፎች ለውድድር መቅረባቸው ታውቋል።

ከግንቦት 02 እስከ 05/2016 ዓ.ም እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የሮቦቲክስ ውድድር ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች የሚያሸንፉ ከኾነ በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን ለመቀጠል የሚያስችላቸውን ነፃ የትምህርት እድል እንደሚያገኙ ተገልጿል።

የሮቦፌስት ውድድር በሎረንስ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በአሜሪካን ሚችጋን ክፍለ ግዛት ውስጥ የሚሰጥ ዓለም አቀፍ ውድድር ሲኾን ዋነኛ ዓላማውም ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን በማበልጸግ ዝንባሌው ያላቸውን ታዳጊ ሕጻናት በዘርፉ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሸጋገር እንደኾነ ተገልጿል።

ኢዜአ እንደዘገበው ውድድሩን እና ተወዳዳሪዎችን በተመለከተ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት ያስተላለፉት በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር እና የሕግ ባለሙያው ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም የመደመር ትውልድ ልጆች ሀገራቸውን የሚያስጠራ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዓላማችን በሀገሪቱ ከፍተኛውን ውጤት ማስመዝገብ ነው” የሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች
Next articleዘርን ከታወቀ ምርጥ ዘር አቅራቢ በመግዛት ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡