“ዓላማችን በሀገሪቱ ከፍተኛውን ውጤት ማስመዝገብ ነው” የሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች

25

ባሕር ዳር: ግንቦት 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ የ12ኛ ክፍል ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠት ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ከሚያስመዘግቡት ይልቅ የማያስመዘግቡት ተማሪዎች በብዙ እጥፍ ይልቃሉ። አንድም ተማሪ ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶች ብዙ ናቸው። ብዙዎች አዲስ የመጣው የፈተና አሰጣጥ ወጀብ ኾኖ ሲያስቀራቸው፣ ጥቂቶች ደግሞ ወጀቡን ተቋቁመው ወደቀጣዩ ዙር አልፈዋል።

ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውጤት ማምጣት ባልተቻለባቸው ዓመታት ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ እና ሁሉንም ተማሪዎች በማሳለፍ ቀዳሚዎች ኾነዋል። በአማራ ክልል የሚገኙ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በተከታታይ ዓመታት በልዩ ሁኔታ በተሰጠው የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ሁሉንም ተማሪዎቻቸውን በማሳለፍ እና ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ብቃታቸውን አሳይተዋል። በልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የታየው መልካም ውጤት ለቀጣይ ትልቅ ተስፋ አሳይቷል። ኩራትም ኾኗል።

በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኘው የሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ባለፈው ዓመት በተሰጠው ፈተና ሁሉንም ተማሪዎቹን በማሳለፍ እና በማኅበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ እንደ ሀገር ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ ስሙ ይጠቀሳል። በትምህርት ቤቱ የተመዘገበውን ውጤት ለማስቀጠል ለዘንድሮው የብሔራዊ ፈተና ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ትምህርት ቤቱ አስታውቋል።

በሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪው አማኑኤል ጫኔ ከአሁን ቀደም የተመዘገበውን ከፍተኛ ውጤት እንደ አርዓያ በመውሰድ ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ እየተዘጋጁ መኾናቸውን ተናግሯል። ለፈተናው በቡድን ኾነው የማጥናት ልምድ እንዳላቸውም ገልጿል። ታሪክ ለመድገም እየተዘጋጀን ነው፣ ከባለፈው ዓመት የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ እየተዘጋጀን ነው ይላል።

በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ትምህርት ዘግይተን እንድንጀምር አድርጎናል፣ ነገር ግን መሰናክል በቁጭት ለመሥራት ጥሩ አጋጣሚ ነው፣ በፈተና አልፎ የሚገኝ ውጤት ጣፋጭ ነው፣ ያን ታሳቢ በማድረግ በርትተን እየተማርን ነው፣ አስተማሪዎቻችን የሚያደርጉልን ድጋፍም የሚደነቅ ነው ብሏል።

እንደ ተማሪ የረጅም ጊዜ እቅድ አለን፣ ለሀገራችን የኾነ ነገር ማበርከት፣ ለዘንድሮው ያለን እቅድ ግን ሁላችንም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ማለፍ ነው፣ “ዓላማችን በሀገሪቱ ከፍተኛውን ውጤት ማስመዝገብ ነው”፣ ያለብንን አደራ ለመወጣት ትኩረት ላይ ነን ይላል።

ሌላኛው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ታደሰ አላምንህ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት እያደረግን ነው ብሏል። ዓላማችን በትንሹ የትምህርት ቤቱን ክብረ ወሰን ማስቀጠል ነው፣ ከዚያ ሲያልፍ ግን በሀገሪቱ ከፍተኛውን ውጤት ማስመዝገብ እና የተሻለ ታሪክ መሥራት ነው ይላል።

ከመምህራን ጋር ያለን ግንኙነት እንደ ቤተሰብ ነው፣ ያልተገደበ ድጋፍ ያደርጉልናል፣ የመምህራን ድጋፍ መልካም መኾን ደግሞ የተሻለ ውጤት ለመሥራት ያስችላል ብሏል። በቡድን ማንበብ እና መዘጋጀት ክፍተቶችን ለመሙላት እንደሚያስችል ነው የተናገረው።

የሐዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ደረጀ ከፈለኝ ተማሪዎችን ለውጤት የሚያበቁ ሥራዎችን እየሠራን ነው ብለዋል። የፀጥታ ሁኔታው በሥነ ልቦና ጫና እንዳያሳድርባቸው ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለተማሪዎች የሥነ ልቦና ሥልጠና መስጠታቸውንም ተናግረዋል። የሥነ ልቦና ሥልጠና ለተማሪዎች ውጤታማነት ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ገልጸዋል።

ተማሪዎችን ለፈተና የሚያዘጋጁ ተከታታይነት ያላቸው የሞዴል ፈተናዎች ይሰጣሉም ብለዋል። ተማሪዎች በፀጥታ ምክንያት ዘግይተው በመጀመራቸው ብሔራዊ ፈተናውን የሚወስዱት በሁለተኛው ዙር መኾኑን ነው የተናገሩት። በየምዕራፎች መጨረሻ ካሁን በፊት የተሰጡ የመግቢያ ፈተናዎችን እንደሚሠሩላቸውም ገልጸዋል።

የተማሪዎች በቡድን መዘጋጀት እና የመምህራን ትጋት ባለፈው ዓመት ስኬት ማስገኘቱን ያስታወሱት ርእሰ መምህሩ ስኬቱን ለማስቀጠል የስኬት ምስጢሮችን አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት። የተማሪዎች እና የመምህራን ግንኙነት ጠንካራ መኾን ለተሻለ ውጤት እንደሚያበቃ ነው የተናገሩት። ችግሮች ላይ ብቻ ማሳበብ አያስፈልግም፣ ተማሪዎች እምቅ አቅም አላቸው፣ ይሄን አቅም መጠቀም ነው ዋናው፣ ለእኛ ልጆቻችን ናቸው፣ ግንኙነታችን እንደ ቤተሰብ ነው። የሀገር በቀል እውቀቶችን የትምህርት አንዱ አካል ማድረጋችን በልጆች ሥነ ምግባር እና ውጤት ላይም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት።

ባለፈው ዓመት ያሳካነውን ስኬት ማጣት እና ደረጃችንን መልቀቅ አንፈልግም፣ ባለፈው ዓመት በማኅበራዊ ሳይንስ ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግበን ነበር፣ ዘንድሮ ግን በሁለቱም ከፍተኛውን ውጤት ለማስመዝገብ ነው የምንሠራው፣ ከፍተኛው ውጤት ከእኛ ትምህርት ቤት መውጣት የለብትም ብለን እየሠራ ነው ብለዋል። ፈተናዎች ለውጤት ምርኩዝ መኾን አለባቸው፣ ወርቅም በእሳት ሲፈተን ነው የሚያንጸባርቀው፣ በዚህ ችግር ውስጥ አልፈው ትልቅ ውጤት ማምጣት አለባቸው፣ ችግሮችን በእልህ እና በቁጭት ወደ ውጤት መቀየር አለባቸው፣ እቅዳችን ታላቅ ውጤት ማምጣት ነው ደግሞም እናሳከዋለን ነው ያሉት።

የፀጥታ ሁኔታው ጫናዎች አሉት፣ ነገር ግን ጫናውን ተቋቁመው ከፍተኛ ውጤት እንዲያመጡ ነው ጥረታችን፣ ከዚህ በኋላ ሰላም ይኾናል ብለን እናስባለን፣ ቀሪው ጊዜ የተሻለ ለመዘጋጀት ይረዳል፣ ለሀገር የሚጠቅሙ ልጆችን ነው እያወጣን ያለነው፣ ሀገራችን ሰላም እንድትኾን እንሻለን ብለዋል።

ትምህርት የመጀመሪያው የአዕምሮ ሰላምን፣ በመቀጠል የሀገር ሰላምን ይፈልጋል፣ ለሰላም መሥራት ጥሩ ነው፣ ነገር ግን በችግር ውስጥም ኾኖ ሀገር፣ ትውልድ ይቀጥላል፣ ችግር እና ሰበብ መደርደር መፍትሔ አያስገኝም፣ መፍትሔ የሚመጣው እድሎችን አሻግሮ በማየት ነው፣ በክልሉ በተፈጠረው ችግር በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል፣ በትምህርት ላይ ያሉ ተማሪዎች ግን ያልተማሩትን ሊያካክስ በሚያስችል መልኩ መታገል እና መሥራት አለባቸው ብለዋል ርእሰ መምህሩ።

እንደ ርዕሰ መምህሩ ገለጻ በታሪክ ብዙ ውጣ ውረዶችን እና የፈተና ጊዜያት አልፈዋል። ይሄም የፈተና ጊዜ ያልፋል። ይሄን በማሰብ እና በማመን መሥራት ይጠበቃል። ችግር ሲያልፍ ግን ትውልድ ጎድቶ እንዳያልፍ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። መምህራን የሚያስተምሯቸውን ተማሪዎች ለማብቃት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፣ ተማሪዎችም በርትተው መሥራት አለባቸው፣ የሚመለከታቸው አካላት ደግሞ ሀገር ሰላም ኾኖ ሁሉም ተማሪዎች እንዲማሩ መሥራት አለባቸው ነው ያሉት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleውኃ አዘል መሬቶችን ከጉዳት ለመከላከል ፖሊሲ እና አዋጅ ሊወጣ መኾኑን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ገለጸ፡፡
Next articleኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በአሜሪካ እየተካሄደ በሚገኘው የሮቦፌስት ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡