
ባሕር ዳር: ግንቦት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ ለውኃ አዘል መሬቶች ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ የሚያስችል ፖሊሲ እና አዋጅ እያዘጋጀ መኾኑን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ገልጿል። በኢትዮጵያ ውኃ አዘል መሬቶች በእርሻ ሥራ፣ በግጦሽ እና ሌሎች ተግባራት ምክንያት ችግር ውስጥ እየገቡ እንደኾኑ የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
የውኃ አዘል መሬቶች ለአካባቢ ሥነ-ምሕዳር እና ለተፈጥሮ ሚዛን መጠበቅ አይተኬ ሚና እንዳላቸው ይወሳል። የዘርፉ ምሁራን የውኃ አዘል መሬቶችን ከአደጋ ለመጠበቅ እና ተገቢውን የአጠቃቀም ሥርዓት ለመተግበር የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልጋቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይስተዋላል።
ጉዳዩ የሚመለከተው የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንም የውኃ አዘል መሬቶች አጠቃቀም፣ እንክብካቤ እና ልማት የተመለከተ የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መኾኑን አስታውቋል። በባለሥልጣኑ የውኃማ አካላት እና የውኃ አዘል መሬቶች አጠቃቀም፣ ክትትል እና ቁጥጥር ዴስክ ኀላፊ ዘሪሁን መንገሻ እንዳሉት የውኃ አዘል መሬቶች ለውኃ ሃብት መጎልበት እና ዘላቂነት ዋስትናዎች ናቸው።
ከሀገር ውስጥ የውኃ ሃብት ጥበቃ ባሻገርም ለድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ፍሰትም ሁነኛ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰው፤ የውኃ አዘል መሬት አጠቃቀም እና ልማትን የተመለከተ የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ስለመኾኑ ተናግረዋል። በዚህም ባለሥልጣኑ ውኃ አዘል መሬቶች የሚመሩበት የአሠራር ሥርዓት እና የሚዳኙበት ረቂቅ ፖሊሲ እና አዋጅ እየተዘጋጀ መኾኑን ተናግረዋል።
የሕግ ማዕቀፉ ተግባራዊ ከተደረገ የውኃ አዘል መሬቶች መመናመን እና መጎዳት ሳቢያ ቀጥተኛ ተፅዕኖ የሚያርፍባቸው የውኃማ አካላትን ብክለት እና ሥነ ምህዳር መመናመንን ለመከላከል ያግዛል ብለዋል። ኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ በአካባቢ ጥበቃ እና ልማት ላይ የምታከናውናቸውን ሥራዎች ለውኃ አዘል መሬቶች ደኅንነት እና ለድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ፍሰት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል። ኢዜአ እንደዘገበው በተለይም ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የውኃ ምንጭ በመኾኗ ለዘላቂ የተፋሰስ ልማት እና የውኃ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች ሀገራቱ ማገዝ እንደሚገባቸው አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!