ለአማራ ክልል ቴክኖሎጂን የሚያዘምኑ ቁሶችን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድጋፍ አደረገ፡፡

31

ባሕር ዳር: ግንቦት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቪድዮ ኮንፈረንስ ካሜራዎች ድጋፍ በክልሉ የሚከናወኑ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሥራዎችን በማጠናከር ውጤታማ ለማድረግ ያለመ ነው። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በክልሎች የሚከናወኑ የዘርፉን ሥራዎች ለማጠናከር የቁሳቁስ፣ የአቅም ግንባታ እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ መኾኑን በመጥቀስ ይህ የቪድዮ ኮንፈረንስ ካሜራ ድጋፍ ለሁሉም ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ተደራሽ መደረጉን ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በቀጣይ በክልሎች በድጋፍ የሚሠሩ የኢኖቬሽን፣ የቴክኖሎጂ እና የዲጂታላይዜሽን ሥራዎችን ለማጠናከር ፕሮጀክቶችን በመንደፍ እንደሚሠራም አንስተዋል። በአማራ ክልል በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪና የከተሞች እና መሰረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አህመዲን መሐመድ (ዶ.ር) ድጋፉ በክልሉ ከተሞች የሚሠሩ ሥራዎችን ለማጠናከር ይረዳል ብለዋል።

የቪድዮ ኮንፈረንስ ካሜራዎች ከኢንተርኔት ውጭም አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ሲኾን ተቋማት ካሉበት ኾነው በማንኛውም ሰዓት ሥራቸውን በአውታር መረብ ግንኙነት በማድረግ በቅንጅት እንዲሠሩ የሚያስችል፤ ወጪን እና ጊዜን በመቆጠብ ቅልጥፍናን የሚጨምር፣ የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን የሚቀንስ፣ ሥብሠባዎችን፣ ትምህርት እና ሥልጠናዎችን ባሉበት ለማስኬድ የሚያስችል ነው።

በዚህ ድጋፍ አሁናዊ አማካይ የገበያ ዋጋቸው 25 ሚሊዮን ብር የኾኑ 43 የቪዲዮ ኮንፈረንስ ካሜራዎች ከነተዛማጅ ዕቃዎቻቸው ለክልሉ ተሰጥቷል። ሌሎች ድጋፎችን በተመለከተ ለሁሉም የክልል እና የከተማ አሥተዳደሮች የወረዳ ኔት ተጠቃሚዎች የአውታረመረብ ግንኙነትን የሚያሻሻሉ 500 የሌይር ስሪ ስዊች ቴክኖሎጂ ድጋፍ ባለፈው ዓመት የተደረገ ሲኾን ቴክኖሎጂዎቹን ወደ ሥራ ለማስገባት የዕውቀት ሽግግር እና ሥልጠና ድጋፍም ተሰጥቷል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በግብርና ዘርፍ ያገኘነውን ስኬት በኢንደስትሪው ዘርፍ ለመድገም ትልቅ ትልም አለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
Next articleየአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የህክምና መሣሪያዎች ድጋፍ አገኘ።