
ደብረ ብርሃን: ግንቦት 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለመኸር እርሻ መዘጋጀቱን የከተማ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ገልጿል። የመምሪያው ኀላፊ መርሻ አይሳነው በከተማ አሥተዳደሩ ከ21 ሺህ ስምንት መቶ ሄክታር በላይ መሬት ለእርሻ መዘጋጀቱን ነው ያነሱት።
የተሳካ የግብርና ተግባር እንዲኖር መምሪያው የ2016/17 የምርት ዘመን የሰብል ልማት እና የክረምት ሥራዎች የንቅናቄ መድረክ አዘጋጅቷል። በመድረኩ የተገኙት የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ የግብርና ሥራ በምንም ሁኔታ ለድርድር አይቀርብም፤ በቅንጅት መሥራት አለብን ብለዋል።
በምግብ ራስን ለመቻል ብሎም ለገበያ ለማቅረብ ከመቼውም ጊዜ በላይ የግብርና ሥራውን አጠናክሮ ማስቀጠል ተገቢ መኾኑን ተናግረዋል። ለከተማ አሥተዳደሩ ከ51 ሺህ ኩንታል በላይ የሰዉ ሠራሽ ማዳበሪያ ያስፈልጋል፤ እስካሁንም ከ31ሺህ ኩንታል በላይ ማቅረብ መቻሉን ከከተማ አሥተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘጋቢ፡- ዮናስ ታደሰ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!