የጡት ካንሰር አሳሳቢነት!

31

ባሕር ዳር: ግንቦት 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ካንሰር በሰውነት ውስጥ የሚገኙ ሕዋሳት ከቁጥጥር ውጭ በኾነ እና ባልተለመደ መንገድ በሕዋሳት መባዛት ምክንያት የሚከሰት በሽታ ነው። ከካንሰር በሽታዎች ውስጥ ደግሞ የጡት ካንሰር አንዱ ነው። በሽታው በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ብሎም በኢትየጵያ አሳሳቢ እየኾነ መምጣቱን በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቤተሰብ ሕክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ሰፊ ድልነሳ ገልጸዋል።

ከአጠቃላይ የካንሰር በሽታዎች መካከል የጡት ካንሰር በሞት ምጣኔ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች ደግሞ ቀዳሚውን ደረጃ ይይዛል። የማህጸን በር ካንሰር በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በሽታው በብዛት በሴቶች ላይ የተለመደ ቢኾንም እስከ አንድ በመቶ ወንዶችንም ያጠቃል። ካንሰሩ የሚፈጠረው ደግሞ ጡት ውስጥ ወተት የሚመነጭበት እና ወተቱ ከተመረተ በኋላ ወደ ጡት ጫፍ በሚወስደው ቱቦ ላይ ነው።

ለጡት ካንሰር በሽታ አጋላጭ ከኾኑ መንስኤዎች ውስጥ ሴት መኾን አንዱ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ከ30 ዓመት በኋላ ተጋላጭነታቸው ይጨምራል፡፡ የእድሜ መጨመር፣ በለጋ እድሜያቸው ማለትም ከ12 ዓመት አካባቢ የወር አበባ የሚያዩ እና የወር አበባ አይተው ከሚጨርሱበት ጊዜ በላይ የሚራዘም ከኾነ፣ ከመጠን በላይ ውፍረት፣ በተደጋጋሚ በጨረር የተጋለጠ ከኾነ፣ ጤናማ ያልኾነ አመጋገብ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ከመጠን በላይ አልኮል መጠቀም፣ ጮማ የሚበዛባቸውን ምግቦች ማዘውተር፣ የታሸጉ ምግቦች እና ስኳር የሚበዛባቸውን ነገሮች ማዘውተር ለጡት ካንሰር አጋላጭ መንስኤ ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡

በጡት ላይ የሚከሰት እብጠት፣ የጡት መጠን መለያየት፣ የተለያየ ቀለም ያለው ፈሳሽ ወይንም በብዛት ደም የቀላቀለ ፈሳሽ በጡት ጫፍ መውጣት፣ የጡት ቆዳ አካባቢ ቀለም መቀየር (መጥቆር፣ መቅላት፣ ልሳላሴውን ማጣት)፣ የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ መግባት (መሰርጎድ)፣ ብብት አካባቢም እብጠት መከሰት የመሳሰሉ ምልክቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡

የጡት ካንሰር ምርመራ በተለያዩ መንገዶች ሊካሄድ እንደሚችል ዶክተር ሰፊ ገልጸዋል። የጡት ካንሰር በሽታ ምልክቶችን በባለሙያዎችም ኾነ ስለበሽታው ዕውቅና ካላቸው ደግሞ ታካሚዎችን የመለየት ሥራ መሥራት ይችላሉ። ሁለተኛው የምርመራ ዓይነት ደግሞ ምልክቶች ሳይታዩ መደበኛ በኾነ መንገድ በታካሚው ወይንም በባለሙያ የጡት አካላዊ ምርመራ ማድረግ ነው። አንድ ሴት ተጋላጭነቱ ኖራትም አልኖራትም በየጊዜው አካላዊ ምርመራ ማድርግ እንዳለባት መክረዋል፡፡

በተለይም ታካሚዋ በራሷ አካላዊ ምርመራውን የምታደርግ ከኾነ መስታውት ፊት ለፊት ሁለት እጆቿን ወደ ታች በማድረግ በመቆም፣ ሁለት እጆቿን አንስታ በመደራረብ አንገት ላይ በማድርግ፣ ጡት ላይ እብጠት መኖሩን በመዳሰስ አካላዊ ምርመራ ማድርግ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጅ የሚያጠቡ እናቶች ከኾኑ እና በውፍረት ምክንያት የጡት መጠን ሊጨምር ይችላል፡፡

በተለይም የምታጠባ እናት ከኾነች ካጠባች በኋላ ምርመራውን ብታደርግ ተመራጭ ይኾናል፡፡ የወር አበባ ያየች ሴት ከኾነች ደግሞ የወር አበባ ካየች ከአምስት እስከ ሰባት ቀናት ባሉት ጊዜያት ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ ነው የመከሩት። የሚያጠራጥር ነገር ካዩ ወዲያውኑ ወደ ጤና ተቋም በመሔድ በባለሙያ የታገዘ ምርመራ ማድርግ ይገባል ብለዋል፡፡

ሦስተኛው የምርመራ ዓይነት በመሳሪያ የታገዘ ምርመራ ማድርግ ነው፡፡ ይህ የምርመራ ዓይነት ተጋላጭ ሴቶች የጡት ራጅ ምርመራ የሚያደርጉበት ዘዴ ነው። አራተኛው የአልትራሳውንድ ምርመራ ነው፡፡ ምርመራው ለሁሉም እናቶች ሊሠራ አይችልም። ምርመራው የሚደረገው “ምልክቱ አለ” ተብሎ ከታሰበ በተለይም ደግሞ እብጠት ነገር ከተከሰተ ነው። በጡት ላይ የሚከሰቱ እብጠቶች ሁሉ ካንሰር ሊኾኑ ስለማይችሉ በ‹‹ፓቶሎጅ›› ምርመራ ወይንም ናሙና በመውሰድ በሚደረግ ምርመራ የማረጋገጥ ሥራ ይሠራል፡፡

የጡት ካንሰር ሕክምና፡-
የጡት ካንሰር ሕክምና ለማድረግ የካንሰሩ ዓይነት፣ ደረጃ፣ አጠቃላይ የታካሚው የጤና ሁኔታ እና የእድሜ ልየታ ሥራ ይሠራል፡፡ በዚህም መሠረት ሕክምናው በቀዶ ጥገና፣ በደም ሥር ወይም በአፍ የሚወሰድ መድኃኒት እና የጨረር ሕክምና እንዲሰጥ ይደረጋል። በመድኃኒት ከሚሰጡ ሕክምናዎች ውስጥ ኬሞቴራፒ አንዱ ነው፡፡ ሕክምናው እስከ አራተኛ ደረጃዎች የሚሰጥ ነው፡፡ እስከ ደረጃ ሦስት የሚገኙ የካንሰር በሽታዎችን ጨርሶ ማቆም ባይቻል እንኳ ባለበት እንዲቆም ያደርጋል፡፡

ደረጃ አራት ላይ ለደረሰ ካንሰር የሚሰጥ የኬሞቴራፒ ሕክምና ደግሞ የሕመሙን ስቃይ ለመቀነስ የሚያገለግል ነው። ሌላው በአፍ የሚወሰድ ሆርሞናል መድኃኒት ሕክምና ነው፡፡ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የደረሰን የጡት ካንሰር እድገት ለመግታት የሚሰጥ ሕክምና ነው፡፡ ደረጃ አራት ላይ ከደረሰ ደግሞ የሕመም ስቃዩ እንዳይጨምር ይሰጣል፡፡ ሌላኛው “ታሪጌቲንግ ቴራፒ” ሕክምና ሲኾን በብዙ ቦታ ባይሰጥም እንደ ሕክምና አማራጭ ተደርጎ ይወሰዳል።

ሌላኛው ደግሞ የጨረር ሕክምና ነው። ሕክምናው በባለሙያዎች የተለዩ ታካሚዎች የቀዶ ጥገናም ኾነ የመድኃኒት ሕክምና ከወሰዱ በኋላ የሚሰጥ ሕክምና ነው፡፡ ካንሰሩ ተመልሶ እንዳይሰፋ የካንሰር ሕዋሶችን ጨርሶ ለመግደል ከፍተኛ መጠን ያለው ጨረር በመልቀቅ የሚከናወን የሕክምና አይነትም ነው፡፡ በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከጨረር ሕክምና ውጭ ያሉት ሕክምናዎች እየተሰጡ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ተጋላጭነትን ለመከላከል ምን ሊደረግ ይገባል? አመጋገብን ማስተካከል፣ የጨረር ተጋላጭነትን መቀነስ፣ መደበኛ የጡት ካንሰር ምርመራ ማድረግ፣ በሳምንት ሦስት ቀን እስከ 30 ደቂቃ መደበኛ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድርግ፣ አልኮል እና ሲጋራ ማጨስ ማቆም፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና በቤት ውስጥ የሚዘጋጁ ምግቦችን ማዘውተር የጡት ካንሰር በሽታ ተጋላጭነትን ለመከላከል ያስችላል፡፡

የካንሰር ሕክምና አለመዘመን እና በበሽታው ላይ ያለው የማኅበረሰቡ ግንዛቤ ዝቅተኛ በመኾኑ ታካሚዎች ወደ ሕክምና ዘገይተው እንደሚመጡ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓመት በወቅታዊ ሁኔታ የታካሚዎች ቁጥር ቢቀንስም ባለፉት ዓመታት የታካሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ስለ ካንሰር በሽታ ዕውቅና በመፍጠር የማኅበረሰቡን የጤና ንቃተ ኅሊና ማሳደግ ተቀዳሚ ተግባር ሊኾን እንደሚገባ መክረዋል፡፡ በሽታው ከታወቀ ደግሞ ይበልጥ ውስብስብ ወደኾነ ደረጃ ከመሸጋገሩ በፊት ክትትል ማድርግ ይገባል። ትላልቅ የሕክምና ተቋማት ወይም ሆስፒታሎችም ከፈውስ ሕክምና ወጥተው በጤና ማጎልበት፣ በበሽታ መከላከል፣ በፈውስ ሕክምና እና በሕመም ማስታገሻን ስታንዳርድን መሰረት ባደረገ መልኩ ሊሠሩ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መገናኛ ብዙኀን የጋራ መገለጫዎችን በማጉላት የወል ትርክትን መፍጠር ላይ በትኩረት መሥራት አለባቸው” የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ
Next articleከ109 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እያሰራጨ መኾኑን የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ።