“መገናኛ ብዙኀን የጋራ መገለጫዎችን በማጉላት የወል ትርክትን መፍጠር ላይ በትኩረት መሥራት አለባቸው” የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ

36

ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መገናኛ ብዙኀን የሕዝቦችን የጋራ መገለጫዎች አጉልቶ በማሳየት የወል ትርክትን መፍጠር ላይ በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገልጸዋል፡፡አማካሪ ሚኒስትሩ “መገናኛ ብዙኀን ለጋራ ትርክት ግንባታ የሚኖረው ሚና” በሚል መሪ ሃሳብ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ተገኝተው ሃሳባቸውን አካፍለዋል፡፡

በመድረኩም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለረዥም ዘመናት በአብሮነት የኖሩባቸው እና የሚያስተሳስሯቸው የጋራ ባሕል እና እሴቶች እንዳሏቸው አውስተዋል፡፡ በየትኛውም አካባቢ በሚከናወኑ ባሕላዊ ክዋኔዎች ላይ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው እሴቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህን የጋራ መገለጫዎች አጉልቶ በማሳየት የወል ትርክት መፍጠር ላይ ውስንነቶች መኖራቸውን ነው ያስገነዘቡት፡፡

መገናኛ ብዙኀን ከልሂቃን ባለፈ ኅብረተሰቡ በጋራ ተከባብሮ እና ተሰናስሎ ለመኖር ያስቻለውን ማኅበራዊ መስተጋብር እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ሃሳቡን እንዲያካፍል የማድረግ ልማዳቸው ዝቅተኛ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡መገናኛ ብዙኀን የሕዝቦችን አንድነት እና አብሮነት የሚያንጸባርቁ ነባር የጋራ ባሕላዊ መስተጋብሮችን ወደ ፊት በማምጣት የወል ትርክት መፍጠር ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው ነው ያሉት፡፡

በተለይም በሕዝቦች የጋራ ባሕሎች፣ ማኅበራዊ እሴቶች፣ ሀገርን ለመከላከል ያላቸውን ጀግንነት፣ አንዱ ማኅበረሰብ ሌላውን የሚቀበልበት መንገድ እና ሌሎች እሴቶችን በሚገባ ማሳየት እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ፋና ዘግቧል፡፡ ከዚህ ባለፈም በሕዝቦች ባሕላዊ አስተራረስ፣ አልባሳት፣ ምግብ አሠራር፣ በንግድ ልውውጥ እና ሌሎች አጠቃላይ የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ ያሉ የጋራ እሴቶችን ነቅሶ በማውጣት ለኅብረተሰቡ ማሳወቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የጋራ የኾኑ መገለጫ ሃብቶችን በሚገባ በማሳየት የወል ትርክትን መገንባት ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ስንቅ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሞሮኮ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ሁለንተናዊ ግንኘነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተሠራ ነው።
Next articleየጡት ካንሰር አሳሳቢነት!