
ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና በፓርላማው የኢትዮ- ሞሮኮ ወዳጅነት ቡድን በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ከኾኑት ናዚሃ አሎዩ ሙሐመዲ ጋር በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ዲማ ነገዎ (ዶ.ር) የሞሮኮ እና የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ታሪካዊ ነው ብለዋል። ሊቀመንበሩ ጨምረውም የሁለቱን ሀገራት ዜጎች በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በጤና፣ በባሕል፣ በስፖርት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር በማስተሳሰር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር የኾኑት ናዚሃ አሎዩ ሙሀመዲ በትምህርት፣ በባሕል፣ በቱሪዝም ፣በንግድ እና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በዲፕሎማሲያዊ መስኮች የኢትዮጵያ እና ሞሮኮን ትብብር የሚያሳድጉ ሥራዎችን እንደሚሠሩ ተናግረዋል። አምባሳደሩ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት ሞሮኮ እንደምታግዝም ተናግረዋል። አምባሳደሩ ጨምረውም በአሕጉሪቱ ኢትዮጵያ የሞሮኮ ስትራቴጅካዊ አጋር መኾኗን ስለመግለጻቸውም ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘ መረጃ አመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!