የአፕል ልማት በሚፈለገው ልክ ምርታማ እንዲኾን ሊሠራ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

13

ደብረ ብርሃን: ግንቦት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን ከሰብል ልማት ጎን ለጎን አትክልት እና ፍራፍሬ በተለያዩ አካባቢዎች የሚለማ ቢኾንም በግንዛቤ እጥረት እና በትኩረት ማነስ ምክንያት የሚፈለገውን ምርት ማግኘት አለመቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡ በመምሪያው የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ቡድን መሪ አስካለ ይፍሩ እንደገለጹት በዞኑ ከ32 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአትክልት እና ፍራፍሬ የለማ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ 3 ሺህ 700 ሄክታር በላይ በቋሚ ተክል የተሸፈነ ነው፡፡

በዞኑ ከሚገኙ 23 የገጠር ወረዳዎች ውስጥ 12ቱ የአፕል ልማት የሚገኝባቸው እንደኾኑ የገለጹት ቡድን መሪዋ በጅምር ደረጃ የተሻለ ምርት ያለባቸው አካባቢዎች መኖራቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡ ለ2016 የክረምት ወቅት ከ73 ሺህ በላይ የአፕል ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውም ተገልጿል፡፡ ከግንዛቤ እጥረት ጀምሮ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትም ከክልል ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር ለዚህ ልማት በተመረጡ ወረዳዎች በዕቅድ ላይ የተመሰረቱ ተግባራትን ለማከናወን ጥረት እየተደረገ እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡

ዘጋቢ፡- በላይ ተስፋዬ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleማሽኖችን አስተውሎት ማላበስ
Next articleበተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የኢትዮጵያን መንግሥት አመሰገነ።