
ባሕር ዳር: ግንቦት 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አሁን ላይ ማሽኖችን በማለማመድ የሰውን አስተውሎት እንዲላበሱ በማድረግ ሥራን እንዲያቀሉ ማድረግ ተችሏል። ይኽን ማድረግ የሚያስችለን ደግሞ “ማሽን ለርኒንግ” ይባላል። በማሽን ለርኒንግ ሥር ደግሞ “ዲፕ ለርኒንግ” የሚባል ንዑስ ክፍል እናገኛለን። ውስብስብ የኾኑ ተግባራትን አስተውሎት ባላበስናቸው ማሽኖች አማካኝነት ማከናወን የምንችልበት ነው።
ዲፕ ለርኒንግ የማሽን ለርኒንግ እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት አንድ ክፍል ነው። ሰዎች በምን ዓይነት መንገድ እውቀትን ያገኛሉ ከሚለው ጽንሰ ሃሳብ የሚቀዳ ነው። ትልቅ መጠን ያለውን መረጃ በዓይነት ለመከፋፈል፣ ፎቶግራፎችን በባሕርያቸው ለመለየት፣ ጽሑፎችን፣ ድምጾችን እና ቪዲዮዎችን ለማደራጀት እና ለመመደብ ያግዛል። የሰው ልጅ ሊሠራቸው የሚችላቸውን ተግባራት በማሽኖች ለመቀየር ያግዟል።
ዲፕ ለርኒንግ የዳታ ሳይንስ በጣም ጠቃሚ የኾነ ንዑስ ክፍል ነው። በጣም ትልቅ መጠን ያላቸውን መረጃዎች የሚሰበስቡ፣ የሚተነትኑ እና የሚተረጉሙ የዳታ ሳይንስ ተመራማሪዎች ዲፕ ለርኒንግ ሥራቸውን ቀላል እና ፈጣን በማድረግ ትልቅ ጠቀሜታ ይሰጣቸዋል። የሰው ልጅ አዕምሮ የተሳሰሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እና በትብብር የሚሠሩ የነርቭ ሕዋሳት እንዳሏቸው ሁሉ የዲፕ ለርኒንግ ኒውራል ኔትወርክ ስልተቀመር በተለያዩ መደቦች የተደራጁ መዋቅሮች አሉት።
የዲፕ ለርኒንግ ሞዴል ኒውራል ኔትወርክ የሚባል ስልተቀመር የሚጠቀም ሲኾን በጣም ትልቅ የኾነ ዴታሴት ይፈልጋል። ዲፕ ለርኒንግ ኮምፒውተራችን ነገሮችን እንዲረዳ ምሳሌዎችን ይጠቁማል። ይኽ ኮምፒውተርን የማስተማር ሂደት ማሽን ለርኒንግ ይባላል። ይህን በቀላሉ ለመረዳት አንድ ሕጻን አፉን እንዲፈታ አንድን ነገር በመጠቆም እና ስያሜውን በመጥራት የማለማመድ እና የማስተማር ሂደት እንደምንከተል አድርገን ማሰብ ነው። በዚህ የማስተማር ሥርዓት ሕጻኑ የዛን ነገር ስያሜ እና ባሕርያቱን ማወቅ ይጀመራል።
በዲፕ ለርኒንግ ማሽኖችን የማስተማር ሂደትም ኮምፒውተራችን በምንሰጠው የማለማመጃ መረጃ የምንፈልገውን መረጃ ተረድቶ ውጤት ያወጣልናል። ዲፕ ለርኒንግ በጣም ብዙ በዓይነት የተደራጀ መረጃ እና መረጃውን ተረድቶ የመተንተን አቅም ይፈልጋል። በዚህ ቴክኖጅ የተጭበረበሩ ሰነዶችን፣ የፊት ገፅታን፣ የሀሰት ዘገባን ለመለየት እና መሰል ተግባራትን ለማከናውን ያግዛል።
ኮማሽን ለርኒንግ ውስጥ የዲፕ ለርኒንግን ያክል ትክክለኛ ውጤትን የማምጣት አቅም ያለው ሌላ ዘርፍ ባለመኖሩ አገልግሎቱን ለሰው አልባ ተሽከርካሪዎች እና በሕክምና ዘርፍ አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ይደረጋል። ኒውራል ኔትወርክ የተሰኘን ስልተቀመር የሚጠቀመው ዲፕ ለርኒንግ ሦስት መሰረታዊ ክፍሎች አሉት።
ግብዓትን የሚሰጥ፣ መረጃዎችን በአመክንዮ የሚተነትን እና የሚረዳ እና ውጤት የሚያወጣልን ክፍል ናቸው። አንድን እንዲደራጅ እና እንዲለይ የምንፈልገውን መረጃ በግብዓትነት እንሰጣለን፣ የተቀበለውን መረጃ ተረድቶ ተንትኖ የተለየ፣ የተደራጀ እና ትክክለኛ የኾነ ውጤትን ይፈጥርልናል። በተለያዩ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ መስኮች ውጤት እያመጣ የሚገኝ ዘርፍ ነው። ለአብነት በኮምፒውተር ቪዥን፣ በተፈጥሮ ቋንቋ ቅንብር እና በንግግር ማወቂያ አገልግሎቶች ላይ እየዋለ እና እያገዘ ይገኛል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!