“በ747 ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ላይ ጥገና ተሠርቷል” የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ

34

ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ጥንታዊ የኾኑ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርሶች በስፋት ይገኛሉ። ታላላቅ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ሥፍራዎች ያሉበት የአማራ ክልል በታላላቅ ሥፍራዎቹ የበዙ ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች አሉት።

እድሜ ጠገብ የኾኑት ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች ተጨማሪ ዘመናትን ተሻግረው ለትውልድ እንዲደርሱ እንክብካቤ፣ ጥበቃ እና ጥገና ያስፈልጋቸዋል። የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ደግሞ ቅርሶችን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ እየሠራ መኾኑን ገልጿል።

የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸሙን በገመገመበት ወቅት የተንቀሳቃሽ እና የቋሚ ቅርሶችን መጠገኑን አስታውቋል። በክልሉ 210 ቅርሶች ላይ የጉዳት መጠን ልየታ በማካሄድ በ25 ቋሚ ቅርሶች ላይ የጥገና ሥራ ለመሥራት ታቅዶ በ131 ቅርሶች የጉዳት ልየታ ተደርጓል ነው የተባለው። 87 ቅርሶች ላይ የጥገና እና የክትትል ሥራ ተሠርቷል ተብሏል።

ለ432 ተንቀሳቃሽ ቅርሶች የጥገና ሥራ ለመሥራት ታቅዶ ለ747 ተንቀሳቃሽ ቅርሶች የጥገና ሥራ እንደተሠራም ተገልጿል። በተንቀሳቃሽ ቅርሶች ላይ የተሠራው ሥራ ከእቅዱ በላይ መኾኑ ተብራርቷል። በ453 ቋሚ እና በ13ሺህ 141 ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ላይ የጽዳት እና የእንክብካቤ ሥራ ተሠርቷል ነው የተባለው። የስዕል ቅርስ ጥገና እየተደረገ መኾኑም ተገልጿል። ለቅርሶች የይዞታ ማረጋገጫ የመስጠት እና የወሰን ክለላ ሥራም ተሠርቷል።

በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰበት የደሴ ሙዚየም ጥገና እና መልሶ የማደራጀት ሥራ ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገበት ነው ተብሏል። በሃይማኖት ተቋማት የሙዚዬም ግንባታ እየተካሄደ መኾኑንም ተመላክቷል። 26 የማይዳሰሱ ባሕላዊ ቅርሶችን ለመመዝገብ ታቅዶ 24 የማይዳሰሱ ባሕላዊ ቅርሶች ተመዝገበዋል ነው የተባለው። የጣና ገዳማትን፣ ባሕረ ደሴትን እና ረግረግ መሬቶችን በዩኒስኮ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሠራ ነው ተብሏል። በጣና ሐይቅ ደሴት ገዳማት እና አዋሳኝ ባሕር ሸሽ መልክዓ ምድር ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርስ ስር የተከለከሉ ሥፍራዎችን ሊያመላክት የሚያስችል ረቂቅ ደንብ እየተዘጋጀ መኾኑም ተመላክቷል።

የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመቀነስ የሚያስችሉ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን መሥራቱንም ቢሮው አስታውቋል። የሰላም፣ የመከባበር፣ የመደጋገፍ፣ የመቻቻል እና ሌሎች ጠቃሚ ባሕሎች እንዲስፋፉ እና በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰርጹ እየተሠራ መኾኑም ተገልጿል። የዕደ ጥበብ ሥራዎችን ለማስፋፋት መሠራቱም ተመላክቷል።አዳዲስ የዕደ ጥበብ ማኅበራት መቋቋማቸውም ተገልጿል። ሀገር በቀል እውቀቶችን ለመጠበቅ እየተሠራ መኾኑን ያመላከተው ቢሮው የአማራ ክልል ሽምግልና መማክርት ጉባኤ ለመመስረት የሚያስችል የማስፈጸሚያ ሰነድ ተዘጋጅቷል ብሏል። በቀሪ ጊዜያት መማክርቱን ለመመስረት ይሠራል ነው የተባለው።

ሀገር በቀል እውቀቶችን እና ባሕላዊ እሴቶችን በማጥናት ለማልማት እና ለመጠበቅ ጥናት እየተደረገ መኾኑንም ቢሮው አስታውቋል። በደቅ ደሴት የቅድስት አርሴማ ወደብ ግንባታ ሥራ 97 በመቶ መድረሱን እና በበጀት ዓመቱ እንደሚጠናቀቅም ተገልጿል። የክልሉ መንግሥት ለቅርስ ጥገና በጀት በመመደብ እያሠራ መኾኑም ተመላክቷል።

ክልሉ ካለው የእድሜ ጠገብ ቅርስ ክምችት አንፃር ከፍተኛ የጥገና በጀት እንደሚጠይቅም ተገልጿል። ለጥገና የሚመደበውን በጀት ማሳደግ ይገባልም ተብሏል። በክልሉ ያሉትን የባሕል፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮ ሃብቶችን አልምቶ እና አስተዋውቆ ወደ ቱሪዝም ገበያ ለማስገባት ከፍተኛ በጀት እንደሚጠይቅም ተመላክቷል። ክልሉን በቱሪዝም ገበያ ተወዳዳሪ እና ተመራጭ ለማድረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማዘመን እንደሚገባም ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዲሞክራሲ እሴትን ለመገንባት እና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው” አቶ መለስ ዓለሙ
Next articleሁለተኛው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ