ማኅበረሰቡን ለግጭት የሚዳርጉ አመለካከቶችን እና አስተሳሰቦችን የመቀየር ሥራ እየተሠራ መኾኑን ሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

20

ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶችን ፈትቶ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡን ለግጭት የሚዳርጉ አመለካከቶችን እና አስተሳሰቦችን የመቀየር ሥራ እየተሠራ መኾኑን ሰላም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ፍሬሰንበት ወልደትንሣኤ በሀገሪቱ የተከሰቱ እና እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች መንስኤዎቻቸው በቅርብ ዓመታት የተፈጠሩ ሳይኾኑ ለበርካታ ዘመን ሲንከባለሉ የመጡ ናቸው ብለዋል።

የዜጎች የፍላጎት መለያየት እና መቃረን በሀገሪቱ እየተከሰቱ ካሉ ግጭቶች ጋር የሚያያዝ ነው ያሉት አማካሪው፤ ግጭቶችን ለመፍታት ለግጭት የሚዳርጉ መሠረታዊ ጉዳዮችን የመለየት ሥራ ተሠርቷል፤ የተለያዩ ለግጭት የሚዳርጉ ጉዳዮችም ላይ ማኅበረሰቡን የማወያየት ሥራ በሰፊው እየተሠራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በወሰን፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በተያያዙ ልዩነቶች ላይ የሚታዩ አንዳንድ አለመግባባቶች፣ ጽፈኝነት፣ ድህነት እና የመሳሰሉት እንዳንግባባ ያደረጉን የግጭት መንስኤዎች ናቸው ያሉት አቶ ፍሬሰንበት የግጭት ችግሮችን ለመፍታት ማኅበረሰቡን የሰላም ባለቤት የማድረግ ሥራም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የሰላም ግንባታ እና የሀገራዊ መግባባት ሥራ የአንድ ወቅት ሥራ አይደሉም፤ ይልቁንም ለረዥም ጊዜ የሚሠሩ ቋሚ ሥራዎች ናቸው ብለዋል አማካሪው፡፡ ዘላቂ ሰላምን አስፍኖ ሀገራዊ መግባባት ለማምጣት ለግጭት የሚዳርጉ አስተሳሰቦችን እና አመለካከቶችን የመለወጥ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ግጭቶችን ለመፍታት ማኅበረሰቡ ራሱ የራሱን ችግሮች አይቶ የሚፈታበት፤ ከአቅሙ በላይ የኾነውን ለሚመለከተው የመንግሥት አካል በማቅረብ እንዲቀረፍለት የማድረግ ተግባር እንዲያከናውን የማወያየት ሥራ እየተሠራ ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡ ‹‹ ግጭቶች ቢከሰቱም የግጭት መፍቻ የኾኑ ባሕላዊ እሴቶቻችንን በማዳበር ልንፈታቸው ይገባል›› ብለዋል፡፡

ባሕላዊና ዘመናዊ የግጭት መፍቻ መንገዶችን በማቀናጀት እና በማዳበር ዘላቂ ሰላም ለመገንባት እንዲሁም ሀገራዊ መግባባትን በማኅበረሰቡ ዘንድ ለማስረፅ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ሰላም ጥቂት ሰዎች የሚያመጡት ዋንጫ አይደለም፤ ሁሉንም ማኅበረሰብ ይመለከታል፤ የሰላም ባለቤትም ራሱ ሕዝቡ ነው፤ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚተው አይደለም፤ ከዚህ አኳያ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡ ኢ.ፕ.ድ እንደዘገበው ማኅበረሰቡ ሰላሙን ከሚነሱ አላስፈላጊ አስተሳሰቦች እና አመለካከቶች ራሱን በማራቅ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚኖርበት ተመላክቷል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በግብርናው ዘርፍ ያሳካነውን ምርታማነት በኢንዱስትሪው በመድገም ኢኮኖሚያችን ልናሳድግ ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“የዲሞክራሲ እሴትን ለመገንባት እና ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው” አቶ መለስ ዓለሙ