ኢትዮጵያ የተወሰኑ ኤምባሲዎች በደቦ የሚያወጧቸውን መግለጫዎች እንደማትቀበል ገለጸች።

19

ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተወሰኑ ኤምባሲዎች በደቦ የሚያወጧቸውን መግለጫዎች ኢትዮጵያ እንደማትቀበል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ ዛሬ ግንቦት 01 ቀን 2016 ዓ.ም የሀገሪቱን ዐበይት የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኅን መደበኛ መግለጫ ሰጥተዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባ የሚገኙ የተወሰኑ ኤምባሲዎች በደቦ የሚያወጧቸው የጋራ መግለጫዎች ከተለመደው የዲፕሎማሲ አሠራር ያፈነገጡ መኾናቸውን ገልጸው ባለፈው ሳምንት የዓለም የፕሬስ ቀንን ምክንያት በማድረግ አንዳንድ ኤምባሲዎች በጋራ የሰጡት መግለጫም የዚሁ አካል መኾኑን ጠቅሰዋል ። ኢትዮጵያ የደቦ መግለጫዎችን አትቀበልምም ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሬስ ነጻነት እንዲከበር ጽኑ አቋም እንዳለው እና ከአሁን በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የነባር እና አዳዲስ የዲጂታል ሚዲያዎች ቁጥር መስፋፋት የፕሬስ ነጻነት እያደገ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል። ይኽ መብት ሊከበር እና ሊጠበቅ የሚገባው በሕግ የበላይነት ማዕቀፍ ውስጥ እንደኾነም ተናግረዋል ።

በሳምንቱ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እና ልዑካን ቡድናቸው ናይሮቢ ኬንያ በተካሄደው የዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር ጉባዔ ላይ ተሳትፈው ጠቃሚ መልእክት ማስተላለፋቸውንም ገልጸዋል። ክቡር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በኤል ሳቫዶር አቻቸው ኤሌክሳንድራ ሂል ቲኖኮ ከተመራ ልዑካን ቡድን ጋር ባደረጉት ውይይት ኤል ሳቫዶር በአዲስ አበባ ኤምባሲ ልትከፍት ማቀዷ ይፋ መኾኑን፣ ይኽም አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ለመምጣቱ ተጨማሪ ማረጋጋጫ መኾኑን አውስተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሀገር ውስጥ መፈናቀል መፍትሄዎች ልዩ አማካሪ ሮበርት ፓይፐርን ተቀብለው ማነጋገራቸውን እና ሮበርት ፓይፐር የኢትዮጵያ መንግሥት በርካታ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው መመለስ መቻሉን ማድነቃቸውን አንስተዋል። ኢትዮጵያ እና ተመድ ትብብራቸውን ለማሳደግ መስማማታቸውንም ቃል አቀባዩ አንስተዋል።

በተጨማሪም አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የሱዳን ሪፐብሊክ ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሁሴን አዋድን ተቀብለው አነጋግረዋል። አምባሳደር ሁሴን ኢትዮጵያ በሱዳን ሁለንተናዊ የሰላም ማስፈን ሂደት ውስጥ እየተጫወተችው ያለውን ወሳኝ ሚና አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል። ክቡር አምባሳደር ምስጋኑም ኢትዮጵያ አበርክቶዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። ቃል አቀባዩ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ እና ማብራሪያ መስጠታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰባተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ።
Next article“በግብርናው ዘርፍ ያሳካነውን ምርታማነት በኢንዱስትሪው በመድገም ኢኮኖሚያችን ልናሳድግ ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)