ሰባተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ።

25

ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አይ ካፒታል ከተሰኘ ተቋም ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሰባተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል። በጉባኤው የፉይናንስ አካታችነት፤ የቀጣናው የኢኮኖሚ ጉዞ እና የኢትዮጵያ ትግበራ ይዳሰሳል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን ተለዋዋጭ የፋናንስ ዘርፍ ጫና ለመቆጣጠር ስትራቴጂክ እቅድ በማውጣት ተግባራዊ እያደረገች ነው።

በሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፉን አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት በርካታ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰው በተለይ በሞባይል ባንኪንግ፣ ኢንተርኔት ባንኪን፣ ቴሌ ብርን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶች እየተተገበሩ መኾኑን ገልጸዋል። በስትራቴጂክ እቅዱ በቅርቡ የፋይንስ ዘርፉን ለውጪ ባለሃብቶች የሚከፈት መኾኑን ጠቅሰው የዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማስፋት የሚረዳ መኾኑን ጠቁመዋል። የፋይናንስ ዘርፉን መቀየር እና አዲስ የኢኮኖሚ አጋርነት የማስፋት ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል።

የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ሥራ አሥፈጻሚ ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ.ር) ጉባኤው የፋይናንስ ዘርፉን የወደፊት አቅጣጫ ለማመላከት የሚረዳ ነው። በፋይናንስ ዘርፉ ያሉትን ፖሊሲዎች ሕግ እና ደንብ ለማጥራት አቅጣጫን ለማመላከት ይረዳል ብለዋል፡፡ የፉይናንስ አካታችነት፤ የቀጣናው የኢኮኖሚ ጉዞ እና የኢትዮጵያ ትግበራ በጉባኤው እንደሚዳሰስ ጠቅሰው የካፒታል ገበያ፣ የዲጂታል ፋይናንስ ጉዞ፣ የፋይናንስ ገበያ ሊበራላይዜሽን ዙሪያ ምክክር እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በጉባኤው ለፖሊሲ አውጭዎች እና አጥኝዎች የጥናት ጽሑፎች እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል። በጉባዔው የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ የፋይናንስ ዘርፍ የሥራ መሪዎች፣ የተለያዩ ቴክኖሎጂ ተቋማት እና የካፒታል ገበያ ዘርፍ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአማራ ክልል በቅርቡ የተሳታፊ ልየታ ሥራ እንደሚጀምር ገለጸ፡፡
Next articleኢትዮጵያ የተወሰኑ ኤምባሲዎች በደቦ የሚያወጧቸውን መግለጫዎች እንደማትቀበል ገለጸች።