
ባሕር ዳር: ግንቦት 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ.ር) እንደገለጹት ባለፈው ሳምንት የኮሚሽኑ ልዑካን ወደ ባሕር ዳር ከተማ በመሄድ ከመንግሥት ኀላፊዎች፣ ከሲቪክ ማኅበራት እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በክልሉ በጎንደር፣ በደሴ እና በባሕርዳር የተባባሪ አካላት ሥልጠና ከዚህ ቀደም መከናወኑን አስታውሰው በቅርቡ በክልሉ በሚገኙ አራት አካባቢዎች የተባባሪ አካላት ሥልጠና በመስጠት የተሳታፊ ልየታ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በ10 ክልሎች እና በሁለት ከተማ አሥተዳደሮች የተደረጉ የተሳታፊ አካላት ልየታዎች በአማራ ክልል እና በትግራይ ክልል በነበረው ነባራዊ ሁኔታ መዘግየቱን አስታውሰዋል፡፡ አሁን ላይ በአማራ ክልል የተሳታፊ ልየታ ሥራ ለማከናወን ዝግጅቶች መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ በክልል ደረጃ የሚደረገው ሀገራዊ ምክክር በአዲስ አበባ ከተማ እና በክልሎች ለማድረግም የሎጂስቲክ እና የሌሎች ግብዓቶች ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ክልሎች፣ ከተማ አሥተዳደሮች፣ ሲቪክ ማኅበራት እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምክክሩ እንዲደረግ ለኮሚሽኑ ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረጉ መኾኑን አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደዘገበው የሚዲያ ተቋማት እያንዳንዱን የምክክሩን ሂደት በመዘገብ እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ የላቀ መኾኑን የተናገሩት ዶክተር ዮናስ ሚዲያዎች ባላቸው ተደራሽነት የምክክሩን አስፈላጊነት ደጋግመው ኅብረተሰቡን የማስተማር ሥራዎች እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!