
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአፈር አሲዳማነት በአፈር ውስጥ የሚገኙ እንደ ካልሼም፣ ሶዲየም፣ ማግኒዝየም እና ፖታሽየም የመሳሰሉ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች ታጥበው ሲያልቁ እና በምትኩ እንደ አሉሙኒየም፣ ሃይድሮጅን እና ብረት (አይረን) የመሳሰሉ ንጥረ ነገሮች በአፈር ውስጥ ሲከማቹ የሚፈጠር ችግር ነው፡፡
በሀገሪቱ ሊታረስ ከሚችለው 15 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 43 በመቶው በአሲዳማነት መጠቃቱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፤ ከዚህም ውስጥ 28 በመቶ በጠንካራ አሲዳማነት የተጠቃ ነው፤ የአፈር አሲዳማነቱ ሽፋንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል። የአፈር አሲዳማነት ችግር ምን ያህል ፈታኝ እንደኾነ እና ከታከመ ደግሞ ምርታማነቱ ሊሻሻል እንደሚችል በፎገራ ወረዳ አንጉኮ ቀበሌ ያነጋገርናቸው አርሶ አደር ማንዴ መኳንንት ነግረውናል።
አርሶ አደር ማንዴ እንዳሉት አንድ ሄክታር ተኩል የእርሻ መሬት በአሲዳማነት በመጠቃቱ ምርት መስጠት አቁሞ ነበር። ይሁን እንጅ ከአራት ዓመት በፊት ግማሽ ሄክታሩን መሬት በኖራ በማከማቸው ከጤናማ መሬት በሄክታር ከሚገኘው ተመጣጣኝ ምርት ማግኘት መቻሉን ነግረውናል። በዚህ ዓመትም አንድ ሄክታር መሬት በኖራ ለማከም የኖራ ግዥ ፈጽመዋል። ኖራ ምርታማነትን የመጨመር አቅሙ ከፍተኛ መኾኑን ያነሱት አርሶ አደሩ በአቅርቦት ምክንያት የተጎዳውን መሬት በሙሉ ማከም አለመቻላቸውን ነው የነገሩን።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ባለሙያ አጠቃ አይቸው ከ10 ዓመት በፊት የተጠናውን መረጃ መሠረት አድርገው እንደነገሩን በክልሉ ከሚታረሰው 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታሩ በከፍተኛ እና 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ደግሞ በመካከለኛ አሲዳማነት ተጠቅቷል።
በተለይም ደግሞ ምዕራቡ የክልሉ አካባቢ በተደጋጋሚ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ በመዋሉ እና በተደጋጋሚ በመታረሱ ምክንያት የአፈር መሸርሸር በማጋጠሙ ይበልጥ ተጋላጭ መኾኑን ገልጸዋል። ባለፉት ዓመታት በበጀት እጥረት እና እንደማንኛውም የግብርና ግብዓት ትኩረት ባለመሰጠቱ የአሲዳማ አፈር ልማት ሥራውም ዝቅተኛ መኾኑን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት 89 ሺህ ሄክታር መሬት ለማከም የሚውል ለ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ኖራ 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በጀት እንደሚያስፈልግ ታቅዶ እንደነበር ገልጸዋል። ይሁን እንጅ አሁንም የበጀት ችግር በማጋጠሙ የፌዴራል መንግሥት 623 ሺህ 550 ኩንታል ኖራ ለማቅረብ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በዚህም 20 ሺህ 785 ሄክታር ለማከም የቅድመ ዝግጅት ሥራ አየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
የኖራ አቅርቦቱ በሁለት ዙር እንደሚቀርብ ያነሱት ባለሙያው ይህ ዘገባ እሰከተጠናቀረበት ጊዜ የቀረበው ኖራ 4 ሺህ 300 ኩንታል ብቻ ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ወደ አርሶ አደሩ የተሰራጨው 1 ሺህ 189 ኩንታል ነው። ባለሙያው እንዳሉት በክልሉ በአሲዳማነት በተጠቃ አካባቢ ጥቅም ላይ ከሚውለው ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ 50 በመቶ የሚኾነው አገልግሎት ስለማይሰጥ አርሶ አደሩ ከምክረ ሃሳቡ በላይ ማዳበሪያ እንዲጠቀም ተገድዷል። ይህም አርሶ አደሩን ለከፍተኛ ወጭ ዳርጓል።
የክልሉን የእርሻ መሬት የአሲዳማነት ችግር ለመፍታት እና ምርታማነትን ለማሳደግ ከተፈለገ የደጀንን የኖራ ወፍጮ በሙሉ አቅሙ ወደ ምርት በማስገባት፣ ደጀን ላይ እየተገነባ የሚገኘውን ተጨማሪ ፋብሪካ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ በሙሉ አቅም ወደ ምርት ማስገባት እና የመራቤቴን የኖ ፋብሪካ ሥራ እንዲጀምር ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ ከፍተኛ የኾነ የኖራ ጥሬ እቃ ባለባቸው አካባቢዎችም ተጨማሪ ወፍጮዎችን በማቋቋም ምርቱን በስፋት በማቅረብ የተጉዳውን መሬት ማከም ተቀዳሚ ተግባር ሊኾን እንደሚገባም ነው የገለጹት። በኢትዮጵያ ከሚታረሰው መሬት ውስጥ 43 በመቶ አሲዳማ ኾኗል። 13 ሚሊየን ሄክታር መሬት ደግሞ ጨዋማ በመኾኑ በምርታማነት ላይ አደጋ መደቀናቸው በባለሙያዎች እየተነገረ ነው። የግብርና ሚኒስቴር ለጊዜው አሲዳማ መሬትን ለማከም እየሰራሁ ነው ቢልም ውጤታማ ለመኾን ግን ጊዜ ይፈጅብኛል ብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!