
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ የሱዳን ሪፐብሊክ ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ሁሴን አዋድ ዓሊ መሐመድን ተቀብለው አነጋግረዋል። ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ እና በሱዳን የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ውይይት አድርገዋል።
አምባሳደር ሁሴን አዋድ ዓሊ መሐመድ ኢትዮጵያ በሱዳን ሁለንተናዊ የሰላም ማስፈን ሂደት ውስጥ እየተጫወተችው ያለውን ሚና በማድነቅ፤ በሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ እና ወንድማማቻዊ አጋርነት ላይ የተመሠረተ ወሳኝ ሚናዋን አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የሱዳንን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ እስካሁን የተጫወተችውን ሚና አውስተው አበርክቶዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ የሱዳን ሁሉን አቀፍ የሰላም ሂደት በሱዳናውያን ባለቤትነት እና መሪነት መከናወን አለበት የሚል ጽኑ እምነት እንዳላት ሚኒስትር ድኤታው ገልጸዋል። አምባሳደር ሁሴን አዋድ ዓሊ መሐመድ በቅርቡ የሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኾነው መሾማቸው ይታዎሳል። ኢትዮጵያን የመጀመሪያ የጉብኝታቸው መዳረሻ ማድረጋቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!