
አዲስ አበባ: ሚያዚያ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቶፓን ግራቪቲ ኢትዮጵያ የተሰኘ የሚስጥራዊ ህትመቶች ፋብሪካ ለመገንባት በለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡ በመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሽባታ ሂሮኖ እና ሌሎች ሚኒስትሮች እንዲሁም የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ኢትዮጵያ ለረዢም ዘመናት ጊዜያቸው ባለፈባቸው የህትመት ቴክኖሎጂዎች እና ህትመቶች ስትቸገር ቆይታለች ብለዋል። ይህንን ችግር ለመፍታት ያለመው ፋብሪካ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ አማካኝነት ለዚህ ስኬት መብቃቱን አስገንዝበዋል።
ይህ የፋብሪካ ተከላ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ሀገራት አሁን ካለው የሲቪል አቪየሽን ደረጃ ጋር የተጣጣሙ ደረጃቸውን የጠበቁ እና ጥራት ያላቸው ፓስፖርቶች እንዲሁም ቪዛዎች እና መታወቂያዎች ይዘው መንቀሳቀስ እንዲችሉ ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል። ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ፋይዳዎች የሚያስገኝ እና መሠረት የሚጥል ነው ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እና በጃፓን መካከልም ትልቅ የትብብር ማዕቀፍ መኾኑን ገልጸዋል።
ፓስፖርቶች፣ መታወቂያዎች፣ ቪዛ እና ማስተር ካርዶች እንዲሁም ሌሎች ሚስጥራዊ ህትመቶች በከፍተኛ ጥራት በፋብሪካው ይመረታሉ ያሉት ደግሞ የቶፓን ግራቪቲ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ቃልኪዳን አረጋ ናቸው። ፋብሪካው ኢትዮጵያ ለብዙ ጊዜ ስትቸገርበት የነበረውን የህትመት ጥራት እና ሚስጥራዊነት ችግርን ከመፍታት ባለፈ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪን ያስቀራል ነው ያሉት፡፡ ለዕውቀት እና ለቴክኖሎጂ ሽግግርም አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ ሽግግሩን ከማፋጠኑ በላይም ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ትልቅ ፋይዳ የሚኖረው የኢንቨስትመንት ዘርፍ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!